Friday, January 20, 2012

የሰበር መ/ቁ 42752

የሰበር መ/ቁ 42752
ግንቦት 12 ቀን 2001

ዳኞች፡- 1. መንበረፀሀይ ታደሠ
       2. ሐጎስ ወልዱ
       3. ሒሩት መለሠ
       4. በላቸው አንሺሶ
       5. ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡- እነ ወ/ት ማሜ አሠፋ (36 ሠዎች) ወኪል ትዕግስት ድንቁና
          ተሾመ ሃይሌ ቀረቡ
ተጠሪ፡- ብሔራዊ አስጎብኚ የጉዞ ወኪል (NTO) ጠ/ብርሃኑ ከፍያለው

ፍ ር ድ
      በዚህ መዝገብ የተያዘው የሠራተኞችን ቅነሣ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡
      የአሁኑ አመልካች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድ ባቀረቡት ክስ ተጠሪ ድርጅት ከስሯል በሚል አዲስ መዋቅር አስጠንቶ ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 29(3) ሥር ከተመለከተው ውጪ ቅነሣ በማድረግ የሠጠው ማስጠንቀቂያ ህጋዊ ባለመሆኑ ይታገድልን ብለዋል፡፡

      ተጠሪ ድርጅት ለቀረበበት ክስ በሠጠው መልስ በአ/ቁ 377/96 አንቀጽ 28(1) መሠረት ምርታማነትን ለማሣደግ እና የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ በተዘጋጀው መዋቅር መሠረት መመዘኛውን ባለሟሟላታቸው ቅነሣውን ያካሄደው በማለት ተከራክሯል፡፡
      ክሱ የቀረበለት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ ምርታማነትን ለማሣደግና የአሠራር ዘዴን ለመለወጥ አዲስ መዋቅር ማዘጋጀት መብት ያለው ቢሆንም ከጠቅላላ ሠራተኛ ውስጥ የሚቀነሠው ሠራተኛ 10% እና ከዚያ በላይ ሲሆን በአ/ቁ 377/96 አንቀፅ 29(2) የተከተለ ቅነሣ ማድረግ አለበት፡፡ ተጠሪ ግን ሥርዓቱን ያልተከተለ በመሆኑ በአንቀፅ 29(3) ከሀ-ረ ድረስ ባለው ቅደም ተከተል መሠረት ቅነሣውን አከናውኖ እስከሚያቀርብ ጊዜ ድረስ ለአመልካቾች የአንድ ወር ደመወዝ ይክፈል በማለት ወስኗል፡፡
      ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሠኘት ይግባኙን ለፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ ቅነሣው በአ/ቁ 377/96 አንቀጽ 28(2)(ሐ) መሠረት በተጠናው አዲስ መዋቅር አንድ በአንቀፅ 28(3) ስር እንደተመለከተው የሥራ መደቡ በመሠረዙ አይደለም፡፡ በመሆኑም በአንቀጽ 29(3) ሥር የተመለከተውን መከተል አያስፈልግም በማለት የቦርዱን ውሣኔ ሽሮታል፡፡
      የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውም ይህ ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት በሚል ነው፡፡ ይህ ችሎትም ቅነሣው በአንቀፅ 28(2)(ሐ) መሠረት ስለተደረገ በአዋጁ አንቀፅ 29(3) ሥር የተመለከተውን ቅደም ተከተል መከተል አያስፈልግም በማለት የተሠጠውን የህግ ትርጉም አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሠበር ችሎት ያስቀርባል በማለቱ ተጠሪ ቀርቦ ክርክሩን በቃል አሠምቷል፡፡ ችሎቱም መዝገቡን እንደሚከተለው መርምሯል፡፡
      ከፍ ሲል እንደተመለከተው በዚህ መዝገብ አከራካሪ የሆነው ነጥብ በአ/ቁ 377/96 አንቀፅ 28(2)(ሐ) መሠረት ቅነሣ ሲደረግ በአንቀፅ 29(3) ሥር የተዘረዘሩትን ቅደም ተከተል መከተል ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው ነው፡፡
      በሥር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድም ሆነ በፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በተደረገው ክርክር አመልካች ቅነሣውን ያደረገው ምርታማነትን ለማሣደግና የአሠራር ዘዴን ለመለወጥ አዲስ መዋቅር በማዘጋጀቱ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ቅነሣው በአዋጁ አንቀፅ 28(2)(ሐ) መሠረት መደረጉን ተገንዝበናል፡፡ ተጠሪም አጥብቆ የሚከራከረው አንቀፅ 29(3) ተፈፃሚ የሚሆነው በአንቀፅ 28(1) እና 28(3) መሠረት በሚደረግ ቅነሣ እንጂ በአንቀፅ 28(2)(ሐ) የሚመለከት አይደለም የሚል ነው፡፡ በመሆኑም አንቀጽ 29(3) ተፈፃሚነቱ ለማነው የሚለውን ነጥብ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡
      በአዋጁ አንቀፅ 29 ርዕስ እንደምንረዳው ድንጋጌው የሚመለከተው የሠራተኞችን ቅነሣ ጉዳይ ነው፡፡ የዚሁ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር አንድም የሠራተኞች ቅነሣ ምን ማለት እንደሆነ ትርጓሜውን አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት የሠራተኞች ቅነሣ ማለት በአንቀፅ 28(2) በተጠቀሱት ምክንያቶች ቁጥራቸው ከድርጅቱ ሠራተኞች ቢያንስ 10% የሚያህለውን ወይም የሠራተኞች ቁጥር ከ20 እስከ 50 በሆነው ድርጅት 5 ሠራተኞችን የሚመለከት ከ10 ተከታታይ ቀናት ያላነሠ ጊዜ የሚቆይ ቅነሣ ነው፡፡ በመሆኑም በአንቀፅ 28(2) ሥር በተመለከቱት ሠራተኞቹ የተሠማሩበት ስራ በከፊል ወይም በሙሉ ለዘለቄታው በመዘጋቱ ወይም የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዝ ወይም ደግሞ ምርታማነትን ለማሣደግና አዲስ የአሠራር ለውጥ ለመጠቀም ሲባል በርካታ ሠራተኞች መቀነስ ሲኖርባቸው ቅነሣው በምን ዓይነት ሥርዓት ሊከናወን እንደሚገባ አንቀፅ 29(3) ያመለክታል፡፡ በእርግጥ የዚህ ድንጋጌ መግቢያ በአንቀፅ 28(1) መሠረት የሠራተኞች ቅነሣ ሲደረግ ቅነሣው ከሥር የተቀመጡትን ቅደም ተከተል መከተል አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የድንጋጌው መግቢያ “አንቀፅ 28(1)” በማለት የተገለፀው በአፃፃፍ ግድፈት እንጂ ሊጠቀስ የሚገባው “አንቀፅ 28(2)” መሆኑን ችሎቱ ያምናል፡፡ ለዚህም የሚከተሉት ምክንያቶች ማስቀመጥ ይችላል፡፡ በአንቀፅ 29(3) ሥር የተመለከተው ስርዓት ተፈፃሚ የሚሆነው በአንቀፅ 28(1) በተመለከተው መሠረት ለሚሠናበት ሠራተኛ ነው ማለቱ ትርጉም አይሠጥም፡፡ ምክንያቱም በአንቀፅ 28(1) የሚናገረው አንድን ሠራተኛ በማስጠንቀቂያ ከስራ በማሠናበት ስለሚቻልበት ሁኔታ እንጂ ስለ በርካታ ሠራተኞች ቅነሣ አይደለም አንድ ሠራተኛ የተመደበበትን ሥራ ለመስራት ችሎታው የሌለው በሆነ ጊዜ ወይም በደረሠበት የጤና መታወክ ወይም የአካል ጉዳት ሥራውን ለመስራት ያልቻለ ከሆነ ወይም ድርጅቱ ወደሌላ ቦታ ሲዛወር ሠራተኛው ተዛውሮ ለመስራት ፈቃደኛ ሣይሆን ሲቀር ወይም ሠራተኛው የያዘው የሥራ መደብ ሲሠረዝና ወደ ሌላ ሥራ መደብ ማዛወር ሣይቻል ሲቀር ሠራተኛውን ማስጠንቀቂያ ሠጥቶ የስራ ውሉን ማቋረጥ ይቻላል፡፡ እነዚህ በአንቀፅ 28(1) ሥር የተዘረዘሩትን ምክንያቶች የሚመለከቱት ችግር አለበት የተባለውን ሠራተኛ ብቻ እንጂ ሌሎችን ሠራተኞች ባለመሆኑ ሊሠናበት የሚችለውም ይኸው ሠራተኛ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም አንድን ሠራተኛ ለመሠናበት በአንቀጽ 29(3) ሥር የተመለከቱት በርካታ ሠራተኞች የሚቀነሱበትን ሥርዓት መከተል ተገቢ ነው ማለቱ ትርጉም የሌለው ነው፡፡  በመሆኑም በአንቀፅ 28(1) ሥር የተመለከቱት ምክንያቶች ሲያጋጥሙ ከስራ ለማሠናበት መከተል የሚያስፈልግ ስርዓት ሣይኖር ችግር አለበት የተባለውን አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ሠራተኞች በማስጠንቀቂያ ማሠናበት ይቻላል፡፡
      በሌላ በኩል ግን አንቀፅ 28(2) ሥር የተመለከቱት የስራ ውል ማቋረጫ ምክንያቶች ሠራተኞቹ የሚሠናበቱት የተመደቡበትን ስራ ለመስራት ችሎታ ሣይኖራቸው ቀርቶ ወይም ሥራውን ለመስራት ፈቃደኝነት ጎድሏቸው ሣይሆን ድርጅቱ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ብዛት ያላቸውን ሠራተኞች መቀነስ በመገደዱ ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ሠራተኞች ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሥራ መሠናበት ካለባቸው ሥንብቱ እንዴት መከናወን አለበት የሚለው ቀጥሎ መፍትሄ ማግኘት የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ስለዚህም ህጉ መፍትሔ ማስቀመጥ አስፈልጎታል፡፡ ህጉ ከፍተኛ የምርት ውጤት የሚያሣዩና ችሎታ ያላቸው በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ቅድሚያ ሲሠጣቸው ተመሣሣይ የሥራ ችሎታና ተመሣሣይ የምርት ውጤት የሚያሣዩ ሠራተኞች በሚመለከት ደግሞ በአንቀፅ 29/3/ ሀ-ረ በተዘረዘሩት መሠረት ቅነሣው እንዲካሄድ ያዛል፡፡ በመሆኑም በአንቀፅ 29(3) ሥር የተመለከተው የቅነሣ ስርዓት ተፈፃሚነት የሚኖረው በአንቀፅ 28(2) እና (3) ሥር በተመለከቱት ሁኔታዎች ላይ እንጂ በአንቀፅ 28(1) ሥር ለተመለከቱት ሁኔታዎች አይደለም፡፡ በአጠቃላይ አንቀፅ 28 እና 29 በአንድነት ተገናዝበው ሲታዩ በአንቀፅ 29(3) ሥር የተቀመጠው የቅነሣ ሥርዓት ተፈፃሚ የሚሆነው በአንቀፅ 28(2) መሠረት ለሚደረግ ቅነሣ እንጂ በአንቀፅ 28(1) ሥር ለሚደረግ የሥራ ውል ማቋረጥ አይደለም፡፡
      በእርግጥ በአንቀፅ 28(2)(ሐ) ሥር የድርጅት ምርታማነት ለማሣደግ የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሠራተኛ ቅነሣ ማድረግ የሚቻለው በአንቀፅ 29(3) ሥር በተቀመጠው ቅደም ተከተል ቢሆንም ይህን ቅደም ተከተል መከተል ግድ የሚለው ግን የተቀነሱት ሠራተኞች ብዛት ቢያንስ 10% የሚያህለው ወይም የሠራተኞች ቁጥር ከ20-50 በሆነበት ድርጅት ቢያንስ 5 ሠራተኞች ሲቀነሱ ነው፡፡ በመሆኑም አሠሪው የቅነሣ ቅደም ተከተል አይገባም የሚል ከሆነ የሚቀነሱት ሠራተኞች ብዛት ከላይ ከተመለከተው ቁጥር በታች መሆኑን ማስረዳት መቻል ይኖርበታል፡፡
      ወደተያዘው ጉዳይም ስንመለስ ተጠሪ ሠራተኞቹን በአንቀፅ 28(2)(ሐ) መሠረት የቀነሣቸው ለመሆኑ በቦርድም ሆነ በፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በተደረጉት ክርክሮች ተረጋግጧል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከፍ ሲል በተብራራው ምክንያት የቅነሣ ስርዓቱ ሊከናወን የሚገባው በአዋጁ አንቀፅ 29(3) መሠረት ነው፡፡ ተጠሪ ይህንን የቅነሣ ሥርዓት ልከተል አይገባም ማለት የሚችለው የተቀነሱት ሠራተኞች ቁጥር በአንቀፅ 29(1) ሥር ቅነሣ ነው ለማለት እንዲችል በመስፈርትነት ከተቀመጠው የሠራተኞች ቁጥር በታች ነው የሚለውን ፍሬ ነገር በማስረዳት ብቻ ነው፡፡ ተጠሪ ደግሞ ከሥር ጀምሮ የተሠናበቱት የሠራተኞች ቁጥር በህጉ ከተመለከተው በታች ነው በማለት ያቀረበው ክርክር የለም፡፡ እንደውም አመልካቾች የተቀነሱት ሠራተኞች 30% የሚያህሉ ናቸው በማለት በሠበር ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ የገለፁትን በማስተባበል መልስ አልሠጠም፡፡ ይህም በአመልካቾች የተነገረውን ፍሬ ነገር እንዳመነ የሚያስቆጥረው ነው፡፡
      በአጠቃላይ ተጠሪ የሠራተኞችን ቅነሣ ያደረገው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 28(2)(ሐ) በመሆኑ ቅነሣው ሊደረግ የሚገባው በአንቀፅ 29(3) ሥር የተመለከተውን የቅነሣ ሥርዓት በመከተል በመሆኑ የይግባኝ ሠሚው ፍ/ቤት ተጠሪ በህጉ የተመለከተውን የቅነሣ ቅደም ተከተል መከተል አይገባውም በማለት ለድንጋጌው የሠጠው ትርጉም መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ው ሣ ኔ
1/ የፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 70811 ታህሣስ 5/2001 የሠጠው ውሣኔ ተሽሯል፡፡
2/ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሣኝ ቦርድ በመ/ቁ 350/ቀወ1/2000 22/12/2000 ዓ.ም
   የሠጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡
3/ ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራ ይቻቻሉ፡፡
      መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ለመ/ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡


ራ/ታ 

No comments:

Post a Comment