Friday, January 20, 2012

የሰበር መ/ቁ 43315

የሰ/መ/ቁ. 43315
18/9/2ዐዐ1
ዳኞች፡- አብዱልቃድር መሐመድ
       ሐጎስ ወልዱ
       ሒሩት መለሠ
       በላቸው አንሺሶ
       ሱልጣን አባተማም
አመልካች፡- ብራንድ ኒው የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል ኃ/የተ/የግ/ማኀበር ጠበቃ አቶ ቸርነት ወርዶፋ ቀረቡ፡፡
ተጠሪ፡- አቶ መስፍን ታደሰ አልቀረቡም፡፡
      መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሠጥተናል፡፡
ፍ ር ድ
      ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሆኖ ተጠሪ ከሳሽ ሲሆኑ አመልካች ደግሞ ተከሣሽ ነበር፡፡ የክሱ ምክንያት መጋቢት 7 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የሚመነዘር ቼክ ቁጥር ኤኤ 187877 የሆነ ብር 1ዐዐ,ዐዐዐ /አንድ መቶ ሺህ/ የያዘ ቼክ ሰጥተውኝ ለክፍያ ባንክ ስቀርብ ሂሣቡ ታግዷል በሚል ምክንያት ቼኩ ሳይከፈል ተመልሷል፡፡ ስለዚህ በቼኩ የተመለከተውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፈል በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 286 መሠረት በአጭር ሥነ ሥርዓት ታይቶ እንዲወሰን በማለት ክስ ቀረበ፡፡
      አመልካችም ቼኩ የተሠጠው የካቲት 13 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ለተደረገው እስከቫተር ሽያጭ ውል ስምምነት መነሻ ሆኖ ከሽያጩ ገንዘብ ውስጥ 2ዐዐ,ዐዐዐ ብር በዕለቱ ተከፍሎ ቀሪው 1ዐዐ,ዐዐዐ ብር መጋቢት 12 ቀን 2ዐዐዐ የሚመነዘር ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቼክ መስጠታቸውን በማስመልከት ለመከላከል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
      ግራ ቀኙን ያከራከረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 123416 በሆነው በ12/2/2ዐዐ1 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ለመከላከል እንዲፈቀድ የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበል ክስ የቀረበበትን በቼኩ ላይ የተመለከተውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍል ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የከፍተኛ ፍ/ቤትም በመ/ቁጥር 74146 በ26/5/2ዐዐ1 ዓ.ም. በዋለው ችሎች ውሣኔውን አጽንቶታል፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ውሣኔ ላይ ነው፡፡
      ይህ ፍ/ቤትም አመልካች የግል ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቦ የመታለፉን አግባብነት ለመመርመር ለሰበር እንዲቀርብ ታዞ መጋቢት 9 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. የግራ ቀኙን ክርክር አድምጧል፡፡
      የግራ ቀኙ ክርክር ከዚህ በላይ በአጭሩ የተመዘገበው ሲሆን እኛም ክርክራቸውን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 284 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት በአጭር ሁኔታ በሚወሰኑ ክርክሮች ላይ ስለሚፈፀም ሥነ ሥርዓት በሕጉ የተመለከቱ ሥርዓቶችን መሠረት በማድረግ እንደሚከተለው መርምረናል፡፡
      በመሠረቱ በአጭር ሥነ ሥርዓት ዳኝነት ታይቶ እንዲወሰን ክስ የሚቀርብበት ጊዜ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 285/1/ እንደተመለከተው ከሕጉ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ቁጥር 2 መሠረት ተከሣሽ የሆነው ሰው መጥሪያ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአሥር ቀናት ጊዜ ውስጥ ቀርቦ ክሱን ለመከላከል እንዲፈቀድለት ፍ/ቤቱን ፈቃድ እንዲጠይቅ መደረግ እንዳለበት በሕጉ መሠረት ቼኩ የተሠጠበት ምክንያት የኤክስካቬተር ሽያጭ ውል ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ ለመከላከል እንዲፈቀድለት በቃለ መሐላ የጠየቀ መሆኑን ከክርክሩ መዝገብ መረዳት ተችሏል፡፡ የተጠሪ ዋና ክርክር በቼኩ ላይ ሐተታ ወይም ገደብ የለበትም በማለት ነው፡፡ አመልካች ደግሞ በሽያጩ ውል ላይ የቼክ ቁጥር ተጠቅሶ ውል የተገባ መሆኑን በመግለጽ የሚከራከር ሲሆን በዚህ ፍ/ቤት የቃል ክርክር ጊዜ ተጠሪም ይህ የውል ግንኙነት በመካከላቸው እንዳላቸው አልካዱም፡፡ በመከላከያ ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይም ይህ ግንኙነት መኖሩ እስከተገለፀ ድረስ ምንም እንኳን ቼክ እንደ ገንዘብ ለተለያዩ ሰዎች በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል ባሕርይ ያለው የገንዘብ ሰነድ በመሆኑ ቼክ አከፋፈል ላይ ማንኛውም መቃወሚያ ሊቀርብበት እንደማይችል በንግድ ሕጉ የተደነገገ ሲሆን ሕጉ ለይቶ ባስቀመጣቸው ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የቼክ ክፍያ በማናቸውም ምክንያት ሊቆምና ሊታገድ የማይችል መሆኑ አካከራካሪ አይደለም፡፡ ነገር ግን በባለ ጉዳዮቹ መካከል ግልጽ የሆኑ ሁኔታዎች ወይም ግንኙነቶች በተፈጠሩ ጊዜ ብቻ ይህን መቃወሚያ ለማድረግ እንደሚቻል በን/ሕ/ቁ. 717/1/ ተመልክቷል፡፡ በተያዘው ጉዳይ አመልካች ይህን መሠረት በማድረግ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበውን ጥያቄ ፍ/ቤቱ ያልተቀበለው የቼክ ክርክር በመሆኑ ብቻ የቼክን ባህርይ መሠረት ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ የፈቃድ ጥያቄ ደረጃ ላይ የቼክ ባሕርይ ሳይሆን መታየት ያለበት አመልካች ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ምክንያት ፈቃድ የሚያሰጥ መሆን አለመሆኑን ነው፡፡ ሌላ የፍሬ ነገር ክርክር ከፈቃድ በኋላ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበረውን የሽያጭ ውል ግንኙነት መሠረት በማድረግ ለመከላከል እንዲፈቀድ ፍ/ቤቱን ለመጠየቅ ሕጋዊ ምክንያት አለው፡፡ ሆኖም ፍ/ቤቱ በአጭር ሥነ ሥርዓት እንዲታይ የሚቀርቡ ክሶች አመራር ሥርዓትን ሳይሆን የተከተለው የቼክ ባሕርይን መሠረት በማድረግ ውሣኔ መደምደሚያ ላይ መድረሱ አግባብ ሆኖ አላገኘንም፡፡ ምክንያቱም ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በፍ/ቤቱ አግኝቶ የተጠየቀውን ገንዘብ ላለመክፈል በቂ ምክንያት መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው ፍ/ቤቱ ከአጭር ሥነ ሥርዓት ወደ መደበኛ የክርክር ሥነ ሥርዓት ውስጥ በመግባት ግራ ቀኙን በአግባቡ በማስረጃ ካከራከረ በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ውሣኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡
ው ሣ ኔ
  1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 123416 ጥቅምት 12 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. የሰጠው ውሣኔ እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 74146 ጥር 26 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠው ውሣኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. አመልካች ያለውን መከላከያና ማስረጃ አቅርቦ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን በመደበኛ የክርክር ሥርዓት አከራክሮና ማስረጃ ሰምቶ ተገቢውን ውሣኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በፍ/ሥ/ሥ /ሕ/ቁጥር 341 መሠረት መልሰናል፡፡
  3. ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡ መዝገቡን ዘግተናል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡


ነ/ዓ

No comments:

Post a Comment