Friday, March 6, 2020

አዋጅ ቁጥር 1113/2011 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ


አዋጅ ቁጥር 1113/2011 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
የመደራጀት መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሌሎች መብቶችን ለማስከበር ያለውን ፋይዳ መገንዘብ፤
በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው፣ የመንግሥት አሠራር በግልጽነት፣በተጠያቂነትና በአሳታፊነት እንዲከናወን ለማድረግ የነቃና በነፃነት የተደራጀ ማኅበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በማመን፤
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ለማድረግ የተመቻቸ ምህዳር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን በመረዳት፤
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂነት እና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ድርጅቶቹ ሥራቸውን በሕግ መሠረት መሥራታቸውን መቆጣጠር በማስፈለጉ፤
በሕብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና የበጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን፤
ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በሥራ ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2ዐዐ1 የነበሩበትን ክፍተቶች ለመሸፈን የሚያስችል አዲስ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።


ክፍል አንድ
ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

    ይህ አዋጅ “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

2. ትርጓሜ

  የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፦

1/ “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት” (ከዚህ በኋላ ድርጅት ተብሎ የሚጠራ) ማለት ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሠረት፣ የመንግሥት አካል ያልሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገነ እና ሕጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ አካል ሲሆን፣የሙያ ማኅበራትን፣ የብዙሃን ማህበራትን እና የድርጅቶች ኅብረቶችን ይጨምራል።
2/ “አገር በቀል ድርጅት” ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ ሕጋዊ ሥራን ለመሥራት በዚህ ሕግ መሠረት በኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ ነዋሪ በሆኑ የውጭ ሐገር ዜጎች ወይም በሁለቱ አማካኝነት በጋራ የተቋቋመ ድርጅት ነው።
3/ “የውጭ ድርጅት” ማለት በውጭ አገር ሕግ መሠረት የተቋቋመና በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
4/  ”የበጐ አድራጐት ድርጅት“ ማለት ለጠቅላላው ህዝብ ወይም ለሶስተኛ ወገን መስራትን ዓላማ አድርጐ የተቋቋመ ድርጅት ነው፤
5/ “የሙያ ማኅበር” ማለት አንድን ሙያ መሠረት በማድረግ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ ዓላማውም የአባላቱን መብትና ጥቅም ማስከበር፣ የሙያ ሥነ-ምግባርን ማሳደግ፣ የአባላትን አቅም መገንባት እንዲሁም በሙያቸው ለሕዝብና ለአገር አስተዋጽዖ ማድረግን የሚጨምር ነው።
6/ “ኅብረት” ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ድርጅቶች የሚቋቋም ስብስብ ሲሆን፣ የኅብረት ኅብረቶችን ይጨምራል።
7/ “ቦርድ” ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት የተቋቋመው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ቦርድ ነው።
8/ “የዘርፍ አስተዳዳሪ” ማለት የተለየ ፈቃድ በሚያስፈልጋቸው የሥራ ዘርፎች ለሚሰማሩ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ የሚሰጥ እና ተገቢውን ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ነው።
9/ “ልዩ ፈቃድ”ማለት በአንድ ስራ ላይ ለመሰማራት በህግ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ በሆነ ጊዜ በዚህ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚሰጥ የፈቃድ ዓይነት ነው፤
1ዐ/ “ኤጀንሲ” ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት የተቋቋመው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች
           ኤጀንሲ ነው።

11/ “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 47 የተመለከተው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል የሆነ ክልል ነው።
12/ “ምክር ቤት” ማለት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 85 መሠረት የሚቋቋመው የድርጅቶች ምክር ቤት ነው።
13/ “የኃይማኖት ተቋም” ማለት የአንድ ኃይማኖት ተከታዮች ኃይማኖታቸውን ለማደራጀትና ለማስፋፋት የሚያቋቁሙት ተቋም ሲሆን የበጎ አድራጎት ዓላማዎችን ለማሳካት የተቋቋሙ ወይም የኃይማኖት ተቋሙ የሚያቋቁማቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን አይጨምርም።

14/“የራስ አስተዳደር”ማለት ድርጅቶች በምክር ቤቱ አማካኝነት ራሳቸውን ለማስተዳደር  በፈቋዳቸው በሚያወጡት የሥነ ምግባር ደንብ የሚመራ አስገዳጅ የቁጥጥር ሥርዓት ነው፡፡
15/ “የስራ አመራር አባላት”ማለት ተጠሪነታቸው ለድርጅቱ የበላይ አካል /እንደሁኔታው ለድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ወይም ቦርድ/ ሆኖ የድርጅቱን የሥራ ሂደት እንዲከታተሉና እንዲቆጣጠሩ በድርጅቱ አባላት ወይም በድርጅቱ ቦርድ የተመረጡ ሰዎች ናቸው፡፡

16/ “የሥራ መሪ” ማለት የድርጅቱን የዕለት ከዕለት ሥራ በበላይነት እንዲመራ በውል የተቀጠረና ተጠሪነቱም ለሥራ አመራር ኮሚቴ ወይም ለድርጅቱ ቦርድ የሆነ ግለሰብ ነው፡፡
17/ “ሰው” ማለት ማናቸውም የተፈጥሮ ሰው ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ነው፡፡
18/ በዚህ አዋጅ ውስጥ በወንድ ፆታ የተገለፀው አነጋገር የሴት ፆታንም ያካትታል፡፡
3. የተፈፃሚነት ወሰን

   1/ይህ አዋጅ በሚከተሉት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡-

   ሀ) በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች፣
   ለ) በውጭ ድርጅቶች፣
   ሐ) በውጭ አገር በሚንቀሳቀሱ፣ ክፍለ አህጉራዊ ፣ አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ዓላማን ለመተግበር በተቋቋሙ አገር በቀል ድርጅቶች፣
 መ) በአዲስ አበባ ወይም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች፣
 ሠ) የኃይማኖት ተቋማት በሚያቋቁሟቸው በጎ አድራጎት ድርጅቶች፤
   2/ ለዚህ አንቀፅ ዓላማ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚንቀሳቀስ ድርጅት ማለት የተቋቋማበትን ዋና ስራ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚሰራ፣ ቋሚ የሆነ ቢሮ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ፣ ቋሚ የሆኑ አባላት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች አፍርቶ የሚንቀሳቀስ ወይም የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ቋሚ በሆነ መንገድ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች የሚሰራ ድርጅት ነው፤
   3/ ይህ አዋጅ በሚከተሉት ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፡-
     ሀ) በኃይማኖት ተቋማት፣
     ለ) በዕድር፣ ዕቁብና መሰል ባሕላዊ ስብስቦች፣
    ሐ) በሌላ ሕግ መሠረት በተቋቋሙ ተቋማት።
ክፍል ሁለት
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ

4. መቋቋም
1/ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ (ከዚህ በኋላ “ኤጀንሲ” እየተባለ የሚጠራ) የሕግ ሰውነት ያለው የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
2/ የኤጀንሲው ተጠሪነት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይሆናል።

5. የኤጀንሲው ዓላማዎች

ኤጀንሲው የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፡-
1/ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የመደራጀት መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤
2/ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሠረት ሥራቸውን ማከናወናቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር የሕብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤
3/ ድርጅቶች አቅማቸው እንዲጎለብትና ተልዕኮአቸውን በብቃት እንዲወጡ ማስቻል፤
4/ በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና በጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ፤
5/ ድርጅቶች አሳታፊ የሆነ፣ ግልጽነትና እና ተጠያቂነት የሠፈነበት የውስጥ አስተዳደር እና አሰራር እንዲኖራቸው ማበረታታትና መደገፍ፤
6/ በድርጅቶችና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም የሥራ ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ አሰራሮችን መዘርጋት፤
7/ ለድርጅቶች የራስ ቁጥጥርና አስተዳደር ስርዓት ተገቢውን ድጋፍ መስጠት፡፡
6. የኤጀንሲው ሥልጣንና ተግባራት

ኤጀንሲው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-
1/ በዚህ አዋጅ መሠረት ድርጅቶችን መመዝገብ፣ መደገፍ፣ ሥራቸውን ማሳለጥና ማስተባበር፤
2/ ድርጅቶች ሥራቸውን በሕግ አግባብ ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፤
3/ የድርጅቶችን ዓመታዊ የሥራና የገንዘብ እንቅስቃሴ ሪፖርት በዚህ ሕግ በተወሰነው መሠረት መመርመር፤
4/ ድርጅቶች ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የውስጥ አስተዳደር እና የራስ አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠትና ተፈፃሚነቱን መከታተል፤
5/ ከሚመለከታቸው የክልል መንግስታት አካላት ጋር በመተባበር በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ቁጥር፣ የተሰማሩባቸውን ክልሎችና የሥራ ዘርፎች፣ የተጠቃሚዎቻቸውን እና የአባሎቻቸውን ብዛት እና መሰል መረጃዎች የሚይዝ የመረጃ ማዕከል ማቋቋም እንዲሁም እነዚህን መረጃዎች መተንተንና በጋዜጣና በድረ-ገጽ አሳትሞ ማሰራጨት፤
6/ ከፌደራልና ከክልል የመንግሥት አካላት እንዲሁም ከድርጅቶች ጋር ቋሚ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት፤
7/ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከዘርፍ አስተዳዳሪዎች ጋር በትብብር መሥራት፤8/ ድርጅቶች መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ሕጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት፤
9/ ድርጅቶች በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና የልማት እንቅስቃሴ ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ተገቢውን ጥናት ማካሄድና መንግሥትን ማማከር፤
10/ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች መንግሥት ከሚያወጣቸው የልማት ዕቅዶች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የሚያግዙ የፖሊሲ መመሪያዎችን ማዘጋጀት፤
11/ አግባብነት ባላቸው ሕጎች ስለሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የድርጅቶችን መተዳደሪያ ደንቦችና ማሻሻያዎቻቸውን ማረጋገጥና መመዝገብ፤
12/ የአገልግሎት ክፍያዎችን በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ ደንብ መሰብሰብ፤
13/ የንብረት ባለቤት መሆን፣ ውል መዋዋል፣ በራሱ ሥም መክሰስና መከሰስ፤
14/ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በዚህ አዋጅ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት ለሌሎች አካላት በውክልና መስጠት፤
15/ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን መክፈት፤
16/ በዘርፉ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በትብብር መሥራት፤
17/ ድርጅቶች ሲፈርሱ በሒሳብ አጣሪነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን ዝርዝር ማዘጋጀትና ሥራቸውን ባግባቡ ማከናወናቸውን መቆጣጠር፤
18/ በዚህ አዋጅ የተቋቋመውን የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ ማስተዳደር፤
19/ የበጎ ፈቃደኝነትን ባሕልና እንቅስቃሴ ማበረታታት እና በጐ ፈቃደኝነት በተመለከተ የስርፀት ስራ መስራት ፤
20/ ዓላማውን ለማስፈጸም የሚስፈልጉ ሌሎች ተግባራት ማከናወን።


7. የኤጀንሲው አቋም

ኤጀንሲው፣

1/ ቦርድ ፣
2/ በመንግስት የሚሾም ዋና ዳይሬክተር እና እንደ አስፈላጊነቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ እና
3/ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች ይኖሩታል።
8. የቦርዱ አባላት

1/ ቦርዱ በሚከተለው ሁኔታ የሚሰየሙ አስራ አንድ አባላት ይኖሩታል።
ሀ) በጠቅላይ አቃቤ ህጉ የሚሰየሙ የሦስት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች፣
ለ) በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሚሰየሙ ሦስት ተወካዮች፣
ሐ) በሲቪል ማኅበረሰብ ሥራ ተገቢው ዕውቀትና ልምድ ያለውና በግል ብቃት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሚሾም አንድ ባለሞያ፣
መ/ የሁሉንም አካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም ወይም ተሳትፎ የማሳደግና ማጠናከር ልምድና ችሎታ ያላቸው ሁለት አባላት በራሳቸው በአካል ጉዳተኞች ማህበራት ብሔራዊ ፌዴሬሽን፤
ሠ/ ከሴቶችና ወጣቶች ማህበራት በራሳቸው አደረጃጀቶች የሚወከሉ ሁለት አባላት፤
2/ የቦርድ አባላት ከየትኛውም ዓይነት ተጽዕኖ ነፃ በመሆን ሥራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ያከናውናሉ።
3/ የቦርዱ ሊቀመንበር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሚሾም ሲሆን የሥራ ዘመኑም ሦስት ዓመት ይሆናል።

9. የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር

ቦርዱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1/ የመደራጀት መብትን አፈጻጸም በማጎልበትና በዘርፉ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ኤጀንሲው የሚመራባቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል።
2/ ዋና ዳይሬክተሩ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቀርቡ ይግባኞችን ይመረምራል፣ ውሳኔ ይሠጣል፤አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጉዳዩን የሚመረምር ገለልተኛ አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ ይሰይማል፣ ኮሚቴው በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ መሠረትም አስተዳደራዊ ውሳኔ ይሰጣል።
3/ የአቤቱታ አጣሪ ኮሚቴውን አሰራር የሚወስን መመሪያ ያወጣል።
4/ በዚህ አዋጅ መሠረት ድርጅቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ያወጣል፤ አፈፃፀሙን ይከታተላል።
5/ በዋና ዳይሬክተሩ የሚቀርብለትን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድና ሪፖርት መርምሮ ያጸድቃል።
6/ የዋና ዳይሬክተሩና የምክትል ዋና ዳይሬክተሮች የሥራ አፈጻጸም በየጊዜው ይገመግማል፤ የግምገማውን ውጤት መሠረት በማድረግ ዋና ዳይሬክተሩ ወይም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሠራሩን እንዲያሻሽል ይመክራል።
7/ በዋና ዳይሬክተሩ የሚቀርቡለትን ሌሎች ጉዳዮች መርምሮ ይወስናል።


10. የቦርድ አባላት የሥራ ዘመን

1/ የቦርድ አባላት የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት ሲሆን ለአንድ ተጨማሪ የሥራ ዘመን እንደገና ሊመረጡ ይችላሉ።
2/ የሥራ ዘመኑ ከማለቁ በፊት መልቀቅ የሚፈልግ የቦርድ አባል ጥያቄውን ለቦርዱ በጽሑፍ በማቅረብ መልቀቅ ይችላል።
3/ በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ /1/ የተደነገገው ቢኖርም በዚህ አዋጅ መሠረት ከሚሰየመው የመጀመሪያው ዙር ቦርድ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች ከሚሰየሙ አባላት አንድ አባል እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም በአካል ጉዳተች እና ሴቶችና ወጣቶች ከሚሰየም አባላት መካከል የአንድ አባል በጠቅላላው የሁለት አባላት የስራ ዘመን ለአራት ዓመት ይሆናል ፡፡ የስራ ዘመናቸው ለአራት ዓመት የሆነ አባላት በድጋሚ ሊመረጡ አይችሉም ፡፡
 4/ በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ /3/ መሠረት የሚሾሙ የስራ ዘመናቸው አራት ዓመት የሚሆኑ የቦርድ አባላት መጀመሪያ በጠቅላይ አቃቤ ህጉ ለሹመት በሚቀርቡበት ጊዜ ይለያሉ፡፡

11. የቦርዱ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት

1/ የቦርዱ ሊቀመንበር የቦርዱን ስብሰባ ይመራል። ሊቀመንበሩ በማይገኝበት ጊዜ በስብሰባው የተገኙ አባላት ከመካከላቸው ሰብሳቢውን ይሰይማሉ።
2/ ዋና ዳይሬክተሩ ድምፅ የመስጠት መብት ሳይኖረው በቦርዱ ስብስባ ላይ ይሳተፋል።
3/ የቦርዱ መደበኛ ስብሰባ በየሁለት ወሩ የሚካሄድ ሲሆን እንደአስፈላጊነቱ የቦርዱ ሊቀመንበር ወይም ከቦርድ አባላት 1/3ኛው ከጠየቁ ከዚህ ባነሰ ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባዎችን ሊያደርግ ይችላል።
4/ የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ቦርዱ የራሱን የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

12. የዋና ዳይሬክተሩ ሥልጣንና ተግባር

1. ዋና ዳይሬክተሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ሆኖ፣ ከቦርዱ በሚሰጠው አጠቃላይ መመሪያ መሠረት የኤጀንሲውን ሥራዎች ይመራል፤ ያስተዳድራል።

2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋና ዳይሬክተሩ፡ -

ሀ/ በዚህ አዋጅ ለኤጀንሲው የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት በሥራ ላይ ያውላል፤
ለ/ የኤጀንሲውን ዓመታዊ ሥራ ዕቅድና በጀት ያዘጋጃል፤
ሐ/ በተፈቀደው የኤጀንሲው የሥራና በጀት ዕቅድ መሠረት ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፤
መ/ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ኤጀንሲውን ይወክላል፤
ሠ/ የኤጀንሲውን የሥራ አፈጻጸምና የሒሳብ ሪፖርት ያዘጋጃል፤
ረ/ የኤጀንሲውን ሠራተኞች የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ሕጎችን መሠረታዊ ዓላማዎች ተከትሎ በመንግሥት በልዩ ሁኔታ በሚጸድቅ ደንብ መሠረት ይቀጥራል፤ ያስተዳድራል።

3. ዋና ዳይሬክተሩ ለሥራ ቅልጥፍና በሚያስፈልግ መጠን ሥልጣንና ተግባሩን ለምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዲሁም ለሌሎች የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በውክልና ሊያስተላልፍ ይችላል።

13. የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሥልጣንና ተግባር

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተጠሪነቱ ለዋና ዳይሬክተር ሆኖ፦
1. የኤጀንሲውን ተግባራት በማቀድ፣ በማደራጀት፣ በመምራትና በማስተባበር ዋና ዳይሬክተሩን ይረዳል፤
2. ዋና ዳይሬክተሩ በማይኖርበት ጊዜ ለዳይሬክተሩ የተሰጡትን ሥራዎች ያከናውናል፤
3. በዋና ዳይሬክተሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል።

14. በጀት

የኤጀንሲው በጀት በመንግሥት ይመደባል።

15. የሒሳብ መዛግብት

1. ኤጀንሲው የተሟሉና ትክክለኛ የሆኑ የሒሳብ መዛግብት ይይዛል።
2. የኤጀንሲው የሒሳብ መዛግብትና ሌሎች ገንዘብ ነክ ሰነዶች በዋናው ኦዲተር ወይም በዋናው ኦዲተር በሚሰየም ኦዲተር በየዓመቱ ይመረመራሉ።

ክፍል ሦስት
የድርጅቶች አመሠራረትና ምዝገባ
ንዑስ ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
16. መርሆዎች

የድርጅቶች አመሠራረት በሚከተሉት መርሖች ይመራል:-

1/ ማንኛውም ድርጅት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊቋቋም ይችላል።
2/ በድርጅቶች ውስጥ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ አባል በፈለገ ጊዜ ከድርጅቱ መውጣት ይችላል።
3/ ማንኛውም ድርጅት አግባብነት ያላቸውን ሕጎች መሠረት በማድረግ የአባላት መቀበያ መሥፈርቶችን የመወሰን መብት አለው።
4/ ማንኛውም ሰው የድርጅቱን መስፈርት እስካሟላ ድረስ አባል የመሆን መብት አለው።
5/ እያንዳንዱ አባል እኩል ድምፅ አለው።
6/ ድርጅቶች ለአባላት ትርፍ ለማከፋፈል በማሰብ ሊቋቋሙ አይችሉም።
7/ የድርጅቶች አመሠራረትና የውስጥ አሰራር ዲሞክራሲያዊ መርሖችን የተከተለ፣ ከአድሎአዊነት የፀዳ፣ ነፃና ገለልተኛ ሊሆን ይገባል።
8/ ማንኛውም ድርጅት የሚመራው በመተዳደሪያ ደንቡ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ሙሉ ተሳትፎ በተመረጡ ሰዎች ነው።
9/ ማንኛውም ድርጅት በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ካልሆነ በቀር አባላትን ሊቀበልና ሊያሰናብት አይችልም።
10/ ኤጀንሲው ድርጅቶች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ሞዴል መተዳደሪያ ደንቦችን ያዘጋጃል።

17. የአገር በቀል ድርጅቶች አመሰራረት

ቁጥራቸው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች አገር በቀል ድርጅት ሊመሰርቱ ይችላሉ።

18. የአገር በቀል ድርጅት ዓይነቶች

      ለዚህ ክፍል ዓላማ የአገር በቀል ድርጅት በሚከተለው አይነት አደረጃጀት ሊቋቋም ይችላል።
1/ ማኅበር፣
2/ ቦርድ-መር ድርጅት፣
3/ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት፣
4/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት፣
5/ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ።

ንዑስ ክፍል ሁለት
ማህበርና ቦርድ-መር ድርጅት

19.ማኅበር

1/ ለዚህ ክፍል ዓላማ ማኅበር ማለት፣ ቁጥራቸው አምስት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አባላት የሚቋቋም እና ጠቅላላ ጉባዔው የበላይ ውሳኔ ሰጪ አካል የሆነበት ድርጅት ሲሆን፣ ለዚህ ሕግ አፈጻጸም የሙያ ማኅበራትን ይጨምራል።
2/ አንድ ማኅበር፣ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ሥራ አስኪያጅ፣ ኦዲተርና እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች የሥራ ክፍሎች ያለው ሆኖ ሊደራጅ ይችላል። የማኅበሩ አወቃቀርና አስተዳደር በመተዳደሪያ ደንቡ ይወሰናል።

20. ቦርድ-መር ድርጅት

   1/ ለዚህ ክፍል ዓላማ ቦርድ-መር ድርጅት፣ ቁጥራቸው ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ መሥራቾች የሚቋቋም ሲሆን፣ የድርጅቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ቦርዱ ይሆናል።
  2/ ቦርዱ ቁጥራቸው ከ5 እስከ 13 የሚደርሱ አባላት ይኖሩታል።
  3/ የመጀመሪያዎቹ የቦርዱ አባላት በመመስረቻ ጽሑፉ ላይ በመሥራቾቹ ይሰየማሉ። የቦርድ አባላት የሥራ ዘመንና ከምስረታ በኋላ የቦርድ አባላት የሚሰየሙበት ስርዓት በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል።
 4/ ከድርጅቱ የሥራ መሪዎች ጋር የስጋ እና የጋብቻ ዝምድና ያላቸው ሰዎች የቦርድ አባል መሆን አይችሉም።
 5/ ድርጅቱ ለቦርዱ ተጠሪ የሆነ ሥራ አስኪያጅ እና አስፈላጊው ሰራተኞች ይኖሩታል። ዝርዝሩ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል።
ንዑስ ክፍል ሦስት
የዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅት

21. መሠረቱ

1/ “የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት” ማለት አንድ የተለየ ንብረት፣ ገንዘብ በስጦታ ወይም በኑዛዜ በዘላቂነትና በማይመለስ ሁኔታ ተለይቶ ለተገለጸ የበጎ አድራጎት ዓላማ ብቻ የሚውልበት ድርጅት ነው።
2/  በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ /1/ መሠረት በስጦታ ወይም በኑዛዜ የሚሰጠው የንብረት ወይም የገንዘብ መጠን የበጐ አድራጐት ዓላማውን በመነሻነት ለማሳካት የሚያስችል መሆን አለበት ፡፡
3/ መሥራቹ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ተጠቃሚዎች ይወስናል። መሥራቹ ተጠቃሚዎቹን በበቂ ሁኔታ ካልወሰነ የሥራ አመራር ቦርዱ ከመሥራቹ ሀሳብ ጋር ይስማማል ብሎ በሚገምተው መልኩ ተጠቃሚዎችን ሊወስን ይችላል።

22. ለምዝገባ ስለማመልከት

   1/ መሥራቹ በሕይወት ሳለ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት ምዝገባ የሚጠየቀው በመሥራቹ በራሱ ወይም ለዚህ ጉዳይ በወከለው ሰው ብቻ ነው።
2/ መሥራቹ ከሞተ በኋላ ጥያቄው የሚቀርበው ከመሥራቹ አደራ በተቀበለው ሰው ወይም የመሥራቹን ኑዛዜ በሚያስፈጽሙ ሰዎች ነው።
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) የተጠቀሱት በማይኖሩበት ጊዜ ለዘለቄታ ንብረትን ለበጎ አድራጎት ዓላማ የመስጠት ውል ያዘጋጁ፣ ምስክር የሆኑ ወይም ውሉን በአደራ ያስቀመጡ ሰዎች የምዝገባ ጥያቄ ያቀርባሉ።
   4/ በዚህ አንቀጽ መሠረት ምዝገባ የመጠየቅ ግዴታ የተጣለባቸው ሰዎች ምዝገባውን ሳይጠይቁ የቀሩ እንደሆነ መሥራቹ ከሞተ ከሦስት ወር በኋላ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ማንኛውም ይመለከተኛል በሚል ሰው አመልካችነት ወይም በኤጀንሲው አነሳሽነት ሊመዘገብ ይችላል።
     5/  በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ /4/ መሠረት የሶሶት ወራት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ለበጐ አድራጐት ድርጅት ዓላማው የሚውለውን ገንዘብ ወይም ንብረት እና አጠቃላይ የምዝገባውን አካሄድ አስመልክቶ ዓላማውን የሚፃረር ተግባር ከተፈፀመ ኤጀንሲው በማንኛውም ጊዜ ጣልቃ መግባትና ማስተካከል ይችላል፡፡

23. ንብረትን ለዘለቄታ በጎ አድራጎት ዓላማ የመስጠት ተግባርን መሻር
 ንብረትን ለዘለቄታ በጎ አድራጎት ዓላማ የመስጠት ተግባር በኤጀንሲው ከመመዝገቡ በፊት መሥራቹ ሊሽረው ይችላል።

24. የዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅት አደረጃጀት
       ማናቸውም የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ፣ ሥራ አስኪያጅ፣ ኦዲተርና ሌሎች አስፈላጊ የሥራ ክፍሎች ይኖሩታል።25. የሥራ አመራር ቦርድ ጥንቅር

1/ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በመሥራቹ ወይም እርሱ በወከለው ሰው ይሾማሉ። የቦርድ አባላቱ በዚህ መልክ ካልተሾሙ ኤጀንሲው የሚሾሙበትን መንገድ ያመቻቻል።
2/ አንድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል በማንኛውም ምክንያት ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ በዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አዲስ የቦርድ አባል ይሾማል።
3/ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ቁጥር ከሦስት በታች ሊሆን አይችልም።

26. የሥራ አመራር ቦርድ ሥልጣን እና ተግባር

የሥራ አመራር ቦርዱ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱ የበላይ አካል ሆኖ የሚከተሉት ሥልጣን እና ተግባራት ይኖሩታል፤
1/ የዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን የሚመራ ሥራ አስኪያጅ እና ኦዲተር ይሾማል፤ ያሰናብታል፤
2/ የዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ያስተዳድራል።

27. የሥራ አመራር ቦርዱ ስብሰባዎች

1/ የሥራ አመራር ቦርዱ በዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በተመለከተው መሠረት ይሰበሰባል።
2/ የዘለቄታ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔዎችን የሚያሳልፈው በድምፅ ብልጫ ይሆናል።

28. ለቦርዱ አባላት የሚፈፀሙ ክፍያዎች

1/ በዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ካልተወሰነ በስተቀር አንድ የቦርድ አባል ክፍያ አያገኝም።
2/ በቦርድ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አንድ አባል ያወጣውን ወጪ ለመሸፈን የሚደረግ ማካካሻ እንደ ክፍያ አይቆጠርም።

29. የሥራ አስኪያጁ ሥልጣን እና ተግባር

የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፡-
1/ የዘለቄታ በጎ አድራጎት የድርጅቱን ሥራ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ይመራል፤
2/ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ድርጅቱን ይወክላል፤
3/ የሥራ አመራር ቦርዱ ውሳኔዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ይቆጣጠራል፤
4/ የሥራ ዕቅድና በጀት እንዲሁም የሥራ እና የሒሳብ ሪፖርቶችን ለሥራ አመራር ቦርዱ ያቀርባል፤
5/ የድርጅቱን ገቢ የሚያሳድጉ ሁኔታዎችን ያጠናል፣ በሥራ አመራር ቦርዱ ሲፀድቁም ተግባራዊ ያደርጋል፤
6/ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በድርጅቱ ሥም የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦችን ያንቀሳቅሳል፤
7/ ሌሎች በሥራ አመራር ቦርዱ የሚሰጡትን ተያያዥ ተግባራት ያከናውናል።


30. የኦዲተር ሥልጣን እና ተግባራት

    ኦዲተሩ፡-

1/ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቱን የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ይቆጣጠራል፣
2/ የድርጅቱን የውስጥ ኦዲት ሪፖርት በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባገኙ የሒሳብ አያያዝ መርሆች መሠረት አዘጋጅቶ ለቦርዱ ያቀርባል።

ንዑስ ክፍል አራት
የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት

31. መሰረቱ

ለዚህ ክፍል ዓላማ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት ማለት የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን በሚያቋቁመው ሠነድ መሠረት አንድ የተለየ ንብረት ለበጎ አድራጎት ዓላማ ብቻ እንዲውል በባለአደራዎች የሚተዳደር ድርጅት ነው።

32. አመሰራረት

1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት በስጦታ፣ በኑዛዜ ወይም አግባብ ባለው የመንግስት አካል ውሳኔ ሊቋቋም ይችላል።
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው ስጦታ ወይም ኑዛዜ አግባብ ባላቸው የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ይመራል።
3/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች የሆነ ሰው ማቋቋሚያ ሰነድ፣ መሥራቹን፣ ባለአደራዎቹንና የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ተጠቃሚዎች በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ አለበት።


33. የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት ቀጣይነት

1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊቋቋም ይችላል።
2/ ላልተወሰነ ጊዜ የተቋቋመ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት ዘላቂና የማይሻር ይሆናል።


34. በባለአደራዎች የሚቀርብ የምዝገባ ማመልከቻ

1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች የሆነ ሰው ባለአደራዎቹን መሾም አለበት።
2/ ባለአደራዎች በዚህ አዋጅ አንቀጽ 57 በተደነገገው መሠረት የምዝገባ ምስክር ወረቀት ለማግኘት ለኤጀንሲው የምዝገባ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
3/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት የምዝገባ ጥያቄ ድርጅቱ በተመሠረተ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል።
4/ ባለአደራዎቹ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ከማግኘታቸው በፊት በስጦታው ወይም በኑዛዜው ላይ የተመለከተውን ሀብት ባለይዞታነት ወይም ባለቤትነት ወደ አደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ለማስተላለፍ ከሚያስፈልጉ ድርጊቶች በስተቀር በሀብቱ ላይ ሦስተኛ ወገኖችን የሚያካትት ማናቸውንም ድርጊት መፈፀም አይችሉም።

35. የባለአደራዎች ብዛት

1/ የባለአደራዎች ብዛት ከሦስት ያነሰ እና ከአምስት የበለጠ ሊሆን አይችልም። ከሦስት ያነሱ ሰዎች ተሾመው ከሆነ ይህን መመዘኛ ለማሟላት ኤጀንሲው ቀሪዎቹ ባለአደራዎች የሚሾሙበትን መንገድ ያመቻቻል።
2/ ከአምስት በላይ ባለአደራዎች ተሾመው ከሆነ በቅድሚያ የተጠቀሱት መሥራት የሚችሉና ፈቃደኝነት ያላቸው አምስት ሰዎች ብቻ ባለአደራ ይሆናሉ።
3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው ቢኖርም አንድ ወይም ከዚያ በላይ ድርጅቶች በባለአደራነት ተሾመው ከሆነ የባለአደራዎቹ ብዛት ከሦስት በታች እንዲሆን ኤጀንሲው ሊፈቅድ ይችላል።
4/ በዚህ አንቀጽ መሠረት ከሚሾሙት ባለአደራዎች ቢያንስ አንዱ መደበኛ መኖሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን አለበት።

36. ባለአደራዎች አሿሿም

1/ ባለአደራ የሚሾመው የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ያቋቋመው ሰው ወይም እርሱ የወከለው ሰው ነው። እነዚህ ሰዎች ከሌሉ ኤጀንሲው ባለአደራ የሚሾምበትን መንገድ ያመቻቻል።

2/ የተሾመው ባለአደራ ይህን ኃላፊነት አልቀበልም ካለ ወይም በማናቸውም ምክንያት ባለአደራነቱን ማከናወን ካልቻለ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሌላ ባለአደራ ይሾማል።

37. ድርጅትን በባለአደራነት መሾም

1/ መሥራቹ ሕጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት በባለአደራነት ከሾመ፣ የተሾመው ድርጅት ሥራ መሪዎች የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ያስተዳድራሉ።
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው ድርጅት የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን በኑዛዜው፣ በስጦታው ወይም በኤጀንሲው ትዕዛዝ በተወሰነው መሠረት ከሌሎች ስጦታዎች ወይም ዓላማውን ለማሳካት ከሚጠቀምበት ገቢ ለይቶ በመያዝ ያስተዳድራል።

38. የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት አደረጃጀት

1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅትን ሥራ አስኪያጅ፣ ገንዘብ ያዥ እና ኦዲተር በመሥራቹ ወይም መሥራቹ በወከለው ሰው ይሾማሉ።
2/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱትን ኃላፊዎች መሥራቹ ወይም በመሥራቹ የተወከለው ሰው ያልሾመ እንደሆነ ባለአደራዎቹ ከመካከላቸው ወይም ከውጭ ኃላፊዎቹን ይሰይማሉ።
3/ ባለአደራዎቹ በንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ኃላፊዎቹን ያልሰየሙ እንደሆነ ኃላፊዎቹ በኤጀንሲው ይሾማሉ።
4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰው ቢኖርም፣ ባለአደራዎች ኃላፊነታቸውን በጋራ ያከናውናሉ።
5/ ባለአደራዎቹ ስብሰባቸውን የሚመራ ሊቀመንበር ከመካከላቸው ይመርጣሉ።
39. የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት አስተዳደር

1/ ከባለአደራዎች በጽሑፍ ተቃውሞ እስካልቀረበ ድረስ ሥራ አስኪያጁ የሌሎች ባለአደራዎች ስምምነት ሳያስፈልገው የማስተዳደር ሥራዎችን ይፈጽማል።
2/ ከማስተዳደር ሥራዎች ውጭ ያሉና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ተቃውሞ የቀረበባቸው ውሣኔዎች ከባለአደራዎች ውስጥ ቢያንስ ሦስቱ በተገኙበት ስብሰባ በድምፅ ብልጫ ይወሰናል።
3/ ከባለአደራዎች ውስጥ እኩል ድጋፍ ያላቸው የተለያዩ ሃሣቦች ሲቀርቡ የመጨረሻው ውሣኔ ስብሰባው ሊቀመንበር በሚሰጠው ድምፅ ይወሰናል።
4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) እና (3) መሠረት በተሰጡ ውሳኔዎች የማይስማሙ ባለአደራዎች የልዩነት ሃሣባቸው በቃለ ጉባኤው ላይ እንዲመዘገብላቸው መጠየቅ ይችላሉ።

40. የባለአደራዎቹ ኃላፊነት

1/ ባለአደራዎች ከአንድ መልካም የቤተሰብ አስተዳዳሪ በሚጠበቀው ትጋትና ጥንቃቄ ድርጅቱን ማስተዳደር አለባቸው።
2/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ በተቋቋመበት ሠነድ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በቀር ባለአደራዎቹ ከኤጀንሲው ፈቃድ ውጭ የድርጅቱን ንብረት ለሌላ ሰው ሊያስተላልፉ አይችሉም።
3/ ባለአደራዎች የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ንብረት ያለ ዋጋ ለሌላ ሊያስተላልፉ አይችሉም።
4/ ባለአደራዎቹ በአደራ በጎ አድራጎት ሥራ መሪነታቸው ከሥልጣናቸው በላይ በፈጸሙት ተግባር ወይም በሰጡት ውሳኔ በድርጅቱ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት በአንድነትና በነጠላ ኃላፊ ይሆናሉ። ሆኖም በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት ከውሳኔው መለየቱን ያስመዘገበ ባለአደራ በውሳኔው ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ አይሆንም።

41. የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅትን ስለመወከል

   1/ ሥራ አስኪያጁ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ይወክላል።
  2/ ሥራ አስኪያጁ በርሱ ምትክ ድርጅቱን የሚወክለውን ባለአደራ ይመርጣል፤ ማናቸውም የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ጉዳዮች የሚከታተል ጠበቃ ሊወክል ይችላል።
  3/ ባለአደራዎቹ ከሥልጣን ወሰናቸው ሣያልፉ ለፈፀሟቸው ሕጋዊ ድርጊቶች ተጠያቂ የሚሆነው የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ነው።

42. የማቋቋሚያ ሰነዱ ትዕዛዞች

   1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ካቋቋመው ሰነድ የተቀበላቸውን ግልጽ የሆኑ ትዕዛዞች ባለአደራው መከተል አለበት።

   2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው ቢኖርም በአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ተጠቃሚ ለሆነው ሰው ጥቅም የሚያስፈልግ ሆኖ የታየ እንደሆነ ከተባሉት ትዕዛዞች ውጭ ለመሥራት ባለአደራው ከኤጀንሲው ፈቃድ መጠየቅ ይችላል።


43. ለባለአደራዎች የሚፈፀም ክፍያ

1/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ በተቋቋመበት ሠነድ ወይም በማናቸውም ሌላ ሕግ በግልጽ ካልተመለከተ በስተቀር አንድ ባለአደራ ክፍያ የማግኘት መብት አይኖረውም።
2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም አንድ ባለአደራ ለአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ለሰጠው ወይም የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን በመወከል ለፈጸመው ሙያዊ አገልግሎት ክፍያ ሊፈጸም እንደሚገባ ሁሉም ባለአደራዎች በጽሁፍ ሲስማሙ እና ኤጀንሲው ሲያፀድቅ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሀብት ተመጣጣኝ ክፍያ ያገኛል፤
3/ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ አንድ ባለአደራ በግሉ ያወጣቸው ወጪዎች እንዲተኩለት የመጠየቅ መብት አለው።

44. የባለአደራው ሥራ መልቀቅ

1/ ባለአደራው ሥራ የመልቀቅ ሀሳብ ካለው ሥራውን ከመልቀቁ ከሁለት ወር በፊት ለሌሎች ባለአደራዎች ሊያሳውቅ ይገባል።ይህን ሳያስታውቅ ቢቀር ከዚህ የተነሣ በአደራ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ላይ ለሚደርሰው ኪሣራ ኃላፊ ይሆናል።
2/ ባለአደራው ሥልጣኑን ለሌላ ባለአደራ እስከሚያስተላልፍ ድረስ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን የማስተዳደር ኃላፊነት አለበት።
3/ አንድ ባለአደራ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ከማለፉ አንድ ወር አስቀድሞ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ባቋቋመው ሰው ወይም ይህን ለመፈጸም ሥልጣን በተሰጠው ሰው፤ ወይም እነዚህ ባይኖሩ በኤጀንሲው አዲስ ባለአደራ ይሾማል።

45. የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ንብረት ማስያዝ

1/ የተጠቃሚዎች ባለገንዘቦች የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ንብረት ወይም ተጠቃሚው ሊያገኝ የሚገባውን አበል በማናቸውም ሁኔታ ማስያዝ አይችሉም።

2/ ለተወሰነ ጊዜ የተቋቋመ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲፈርስ ንብረቱን የመውሰድ መብት ያላቸው ባለገንዘቦች የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ንብረት ማስያዝ ይችላሉ።

46. በሽያጭ ስለማስተላለፍ
    ማንኛውም የበጐ አድራጐት ድርጅት ወይም ማህበር ንብረቱን ለሌላ ሦስተኛ ወገን በሽያጭ ሲያስተላልፍ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከቀረጥ ነፃ የገባ ንብረት ከሆነ ሽያጩ በአገሪቱ የጉምሩክ ህግ መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል ፡፡

47. የተጠቃሚዎች መብት

1/ ተጠቃሚዎች በአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ማቋቋሚያ ሠነድ መሠረት የሚገባቸው ጥቅም እንዲሰጣቸው የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ሊጠይቁ ይችላሉ።
2/ ተጠቃሚዎች መብቶቻቸውን የሚጎዳ ሁኔታ ሲፈጠር ባለአደራው እንዲሻር ወይም ተገቢ የሆነ ዋስትና እንዲሰጥ ኤጀንሲውን መጠየቅ ይችላሉ።
3/ ተጠቃሚዎች የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅቱ አካል በሆኑ ንብረቶች ላይ በግልም ሆነ በጋራ የማዘዝ ወይም የማስተዳደር መብት የላቸውም።
4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገገው ቢኖርም እነዚህን ንብረቶች በሚመለከት የይርጋ ዘመን እንዲቋረጥ ማድረግን በመሳሰለው ሥራ መብቶቻቸውን የመጠበቅ ሥራዎችን ብቻ መፈፀም ይችላሉ።

ንዑስ ክፍል አምስት
ስለበጎ አድራጎት ኮሚቴ

48. መሰረቱ

ለዚህ ክፍል ዓላማ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ ማለት ቁጥራቸው አምስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ገንዘብ ወይም ሌላ ንብረት ለበጎ አድራጎት ዓላማ ከሕዝብ ለመሰብሰብ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው።

49. የበጎ አድራጎት ኮሚቴን ስለማፅደቅ

1/ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በኤጀንሲው ሳይፀድቅ ገንዘብም ሆነ ንብረት ማሰባሰብ ወይም ማናቸውም ድርጊት መፈፀም አይችልም።
2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ኮሚቴውን ለማቋቋም በሚደረጉ አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም።
3/ ኤጀንሲው የበጎ አድራጎት ኮሚቴዎችን ሲያፀድቅ የዚህን አዋጅ አንቀጽ 59 እና 62 ድንጋጌዎች በማገናዘብ መወሰን አለበት።


50. የሒሳብ መግለጫ

1. የበጎ አድራጎት ኮሚቴው ዓመታዊ የሒሳብ መግለጫ ለኤጀንሲው ማቅረብ አለበት።
2. የበጎ አድራጎት ኮሚቴው የተቋቋመው ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ ከሆነ ይህ ጊዜ እንዳለቀ የሒሳብ መግለጫ ማቅረብ አለበት።

51. የበጎ አድራጎት ኮሚቴ አደረጃጀት

1/ የበጎ አድራጎት ኮሚቴን የሚያቋቁም ውሳኔ መሥራች አባላቱን፣ የበጎ አድራጎት ኮሚቴውን ፕሬዚዳንት፣ ገንዘብ ያዥና ኦዲተር ዝርዝር ሁኔታ ማሳየት ይኖርበታል።
2/ ውሳኔው የበጎ አድራጎት ኮሚቴውን ዓላማዎች እና ዓላማዎቹን የሚያሳካበትን ጊዜ መግለፅ ይኖርበታል።
3/ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ውሳኔው የበጎ አድራጎት ኮሚቴው ሥራዎች እንዴት መከናወን እንዳለባቸው መወሰን እና በኮሚቴው የሚሰበሰበውን ገንዘብ እና ንብረት መጠንና አጠቃቀሙን ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ማስቀመጥ ይኖርበታል። ዝርዝሩ ኤጀንሲው በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል።

52.የአባላት ኃላፊነት

1/ ከበጎ አድራጎት ኮሚቴው እንቅስቃሴ ለሚመነጩ ግዴታዎችና ዕዳዎች አባላት በአንድነት እና በነጠላ ኃላፊ ይሆናሉ።
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገውን በተመለከተ ኤጀንሲው፣የዘርፍ አስተዳዳሪው፣ ማናቸውም ለጋሽ፣ አባል ወይም ተጠቃሚ፣ በኮሚቴው አባላት ላይ ክስ የማቅረብ መብት አላቸው።

53. በቂ ያልሆነ ገንዘብና ንብረት

1/ በበጎ አድራጎት ኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብና ንብረት የኮሚቴውን ዓላማ ለማሳካት በቂ ካልሆነ ወይም ዓላማውን ማሳካት የማይቻል ከሆነ ይህ ገንዘብ ወይም ንብረት የኮሚቴው መቋቋም በፀደቀበት ውሳኔ ላይ በተመለከተው መሠረት በሥራ ላይ ይውላል።
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 በፀደቀው ውሳኔ ውስጥ የተመለከተ ነገር ከሌለ ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ለስጦታ አድራጊዎቹ ተመላሽ ይሆናል።
3/ ለበጎ አድራጎት ኮሚቴው ገንዘብ ወይም ንብረት የሰጡ ሰዎች መልሰው ሊወስዱት ካልፈለጉ ወይም ካልቻሉ ወይም የማይታወቁ ከሆነ በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት በኤጀንሲው ውሳኔ ለተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ዓላማ ይውላል።

54. ቀሪ ገንዘብና ንብረት

1/ በበጎ አድራጎት ኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብ ወይም ንብረት ዓላማውን ለማሳካት አስፈላጊ ከሆነው በላይ ከሆነ ቀሪው ገንዘብ ወይም ንብረት ኮሚቴው ባፀደቀው ውሳኔ መሠረት ለሌላ ተመሳሳይ የበጐ አድራጐት ዓላማ ሥራ ላይ ይውላል።
2/ በውሳኔው ውስጥ ይህንን በሚመለከት የተገለፀ ነገር የሌለ እንደሆነ ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ኤጀንሲው በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት በኤጀንሲው ውሳኔ ለተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ዓላማ ይውላል።
55. ወደ ዘላቂ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ስለመለወጥ

1/ የበጎ አድራጎት ኮሚቴው በፀደቀበት ውሳኔ ላይ በተመለከተው መሠረት በኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብ ወይም ንብረት ለአንድ ለተወሰነ ዘላቂ ዓላማ የሚውል ከሆነ ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት ዘላቂ የበጎ አድራጎት ድርጅት ይቋቋማል።
2/ በበጎ አድራጎት ኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብ ወይም ንብረት የታቀደውን ዓላማ ለማሳካት አስፈላጊ ከሆነው እጅግ የበዛ ከሆነ የኮሚቴው አባላት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትነት ለመመዝገብ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
3/ ኮሚቴው በድርጅትነት ከተመዘገበ፣ በኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብና ንብረት ወደተመዘገበው ዘላቂ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ይተላለፋል።

ንዑስ ክፍል ስድስት
ኅብረቶችና የኅብረቶቸ ኅብረት

56. ኅብረቶችና የኅብረቶች ኅብረት አመሠራረት

1/ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ወይም ኅብረቶች የጋራ ዓላማቸውን ለማሳካት በመካከላቸው በሚያደርጉት ስምምነት ወይም በዚህ ሕግ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት ኅብረት ወይም የኅብረቶች ኅብረት መመሥረት ይችላሉ።

2/ ኅብረቶች ወይም የኅብረቶች ኅብረት ከአባሎቻቸው መብትና ጥቅም ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት ሊመሠረቱ ይችላሉ፤ ይህም የሚከተሉትን ያካትታል:-

ሀ) ለጋራ ግቦች ስኬታማነት አባሎቻቸውን ማስተባበርና መደገፍ፣
ለ) የሀሳብ፣ የመረጃ እና የልምድ ልውውጥን ማካሄድ፣
ሐ) የአባላትን አቅም መገንባትና ሀብት የማሰባሰብ ጥረታቸውን መደገፍ፣
መ) የአባላትን ሥነ ምግባርና የሙያ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን
ሠ) የአባላት የጋራ ድምፅ በመሆን የአባላትን የጋራ መብትና ጥቅም ማስከበር እና ለአባላት ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠር መሟገት፣
ረ) አባሎቻቸው በተሠማሩበት የሥራ ዘርፍ የጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም የፖሊሲ ሙግት እና ድጋፍ ሥራዎችን ማከናወን፣
    3/ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱት ዓላማዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ማንኛውም ኅብረት አባል ድርጅቱ ከሚሰራበት የሥራ ዘርፍ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሥራ በመሥራት ከአባሉ ጋር ውድድር ውስጥ ሊገባ አይችልም። ሆኖም፣ኅብረቶች ሀብት በማሰባሰብ በአባሎቻቸው አማካኝነት የፕሮጀክት ሥራዎችን ማከናወን ይችላሉ።

ንዑስ ክፍል ስድስት
የድርጅቶች ምዝገባ

57. መሠረቱ
   1/ ማንኛውም ድርጅት በዚህ ሕግ መሠረት በኤጀንሲው መመዝገብ አለበት።
   2/ ኤጀንሲው የአገር በቀል ድርጅት ማመልከቻ በቀረበለት በ30 ቀናት ውስጥ፣ የውጭ ድርጅት ከሆነ ደግሞ የምዝገባ ማመልከቻ ከሥራ እቅድ ጋር በቀረበለት በ45 ቀናት ውስጥ በዚህ አዋጅ የተደነገጉት አስፈላጊ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ አመልካች ድርጅቱን በመመዝገብ የምስክር ወረቀት ይሰጣል።
  3/ አመልካቹ ከላይ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ያልተሰጠው እንደሆነ በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለቦርዱ ማቅረብ ይችላል።
  4/ ቦርዱ የቀረበለትን ቅሬታ በመመርመር በ60 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል።

  5/ ኤጀንሲው ድርጅቱን ያልመዘገበው ያለበቂ ምክንያት መሆኑን ቦርዱ ሲረዳ የምዝገባ ሰርተፊኬቱ ወዲያውኑ እንዲሰጥ ያዛል። ለዚህ ድንጋጌ አፈጻጸም፣ ኤጀንሲው ለቀረበለት የምዝገባ ማመልከቻ በንዑስ አንቀጽ 2 በተመለከተው ጊዜ ምላሽ ካልሰጠ፣ ድርጅቱን ላለመመዝገብ በቂ ምክንያት እንደሌለው ይቆጠራል።
  6/ በቦርዱ ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ አመልካች የቦርዱ ውሳኔ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ይችላል።

58. ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች

    1/ የአገር በቀል ድርጅቶች የምዝገባ ማመልከቻ በድርጅቱ መሥራቾች ሰብሳቢ ተፈርሞ መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ የሚከተሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ማካተት ይኖርበታል: -
ሀ) የመሥራቾችን ሥም፣ አድራሻና ዜግነት የያዘ የምሥረታ ቃለ-ጉባኤ፤
ለ) የመሥራቾች የመታወቂያ ወይም የፓስፖርት ኮፒ፤
ሐ) የድርጅቱን ሥም እንዲሁም ዓርማ (ካለው)፤
መ) የድርጅቱን ዓላማ እና ሊሰማራ ያሰበበትን የሥራ ዘርፍ፤
ሠ) ሊሰማራ ያሰበበትን የሥራ ቦታ (ክልል)፣
ረ) በመሥራቾች የፀደቀ መተዳደሪያ ደንብ፣
ሰ) የድርጅቱን አድራሻ።
   2/ በውጭ አገር የተመሰረተ ድርጅት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ከተደነገጉት
አስፈላጊ ሁኔታዎች በተጨማሪ የሚከተሉትን ማቅረብ ይኖርበታል:-
ሀ) ድርጅቱ መቋቋሙን የሚያሳይ ከተቋቋመበት አገር የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ ሰነድ፣
ለ) ሥልጣን ያለው የድርጅቱ አካል ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ ያሳለፈው በአግባቡ የተረጋገጠ ውሳኔ፤
ሐ) የአገር ውስጥ ተወካዩ የተሠጠው በአግባቡ የተረጋገጠ የውክልና ሥልጣን ከተቋቋመበት አገር ኢምባሲ ወይም ኢምባሲ ከሌለ ከተቋቋመበት አገር ስልጣን ባለው አካል የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ ፣
መ) ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚተገበር የሥራ ዕቅድ።
   3/ የኅብረቶች የምዝገባ ማመልከቻ በተወካያቸው ድርጅት ኃላፊ አማካኝነት ተፈርሞ ከሚከተሉት ሰነዶች ጋር ተያይዞ ይቀርባል፤
ሀ)በኅብረቱ መሥራች ድርጅቶች ተወካዮች የተፈረመ የመተዳደሪያ ደንብ፣
ለ) አባላት ኅብረቱን ለመመስረት የተስማሙበት ቃለ ጉባዔ፣
ሐ) ለኅብረቱ አባላት ከኤጀንሲው ወይም ሥልጣን ካለው የክልል አካል የተሰጠ

የአባላት የምዝገባ የምስክር ወረቀት፣
   4. አመልካቹ አግባብነት ባለው ደንብ የሚወስነውን የምዝገባ ክፍያ ይከፍላል።
   5. የሙያ ማኅበራትን ምዝገባ እና አስተዳደር ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

59 የምዝገባ ጥያቄን ስላለመቀበል

1. ኤጀንሲው ከሚከተሉት ምክንያቶች አንዱ መኖሩን ካረጋገጠ ድርጅቱን አይመዘግብም፡-
    ሀ/ ማመልከቻው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 57 የተደነገጉትን መስፈርቶች የማያሟላ ሆኖ ሲገኝና ይህንንም እንዲያስተካክል የአመልካቹ ተወካይ ተጠይቆ ለማስተካከል ካልቻለ፤
    ለ/ የድርጅቱ ዓላማ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተመለከተው የሥራ ዝርዝር ለሕግ ወይም ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ ከሆነ፣
   ሐ/ ድርጅቱ የሚመዘገብበት ሥም ወይም ዓርማ፣ ከሌላ ድርጅት ወይም ከማንኛውም ሌላ ተቋም ሥም ጋር የሚመሳሰል ከሆነ ወይም ሕግን ወይም የሕዝብን ሞራል የሚቃረን ከሆነ፣
  መ/ ድርጅቱ ለምዝገባ ያቀረበው ሰነድ በሐሰት የተዘጋጀ ወይም የተጭበረበረ ከሆነ።

2. በዚህ ሕግ በግልጽ ከተመለከቱት ምክንያቶች ውጪ ኤጀንሲው በአሰራርም ይሁን መመሪያ በማውጣት የምዝገባ ጥያቄን ሊከለክል አይችልም።
3. ማመልከቻውን በዚህ ሕግ መሠረት መርምሮ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ አመልካቹ የጎደለውን ነገር በ30 ቀናት ውስጥ አስተካክሎ እንዲቀርብ ኤጀንሲው በጽሑፍ መልስ ይሰጠዋል።
4. አመልካቹ የተባለውን ነገር ለማስተካከል ፍቃደኛ ካልሆነ ኤጀንሲው ማመልከቻውን ያልተቀበለበትን ሕጋዊ ምክንያት በመጥቀስ ጥያቄውን ውድቅ ያደርጋል።

5. የምዝገባ ጥያቄው ውድቅ የሆነበት አመልካች በኤጀንሲው ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ቅሬታውን በ30 ቀናት ውስጥ ለቦርዱ ማቅረብ ይችላል።
6. ቦርዱ ቅሬታው በቀረበለት በ60 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል።
7. አንድ ድርጅት በማታለል ወይም በማጭበርበር የምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቶ ከሆነ፣ ይኸው በኤጀንሲው ሲረጋገጥ ቦርዱ ድርጅቱ እንዲፈርስ ሊወስን ይችላል።
8. ከላይ በንዑስ አንቀጽ 6 እና 7 መሠረት በተሰጠ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ድርጅት የቦርዱ ውሳኔ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኙን በመሥራቾቹ አማካኝነት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።60. የመተዳደሪያ ደንብ አስፈላጊነትና ይዘት

    1/ ማንኛውም ድርጅት የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ የመተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው ይገባል፡-
ሀ) የድርጅቱ ሥም፣
ለ) የድርጅቱ ዓላማዎች፣
ሐ) የድርጅቱ የበላይ አካል፣ ሥልጣንና ተግባር፣ የውስጥ አደረጃጀትና አስተዳደር፣ የስብሰባና የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት፣
መ) የድርጅቱ ገቢና ሐብት ለአባላት እንዲሁም ለሠራተኞች በሕግ ከተፈቀደ የአገልግሎት ክፍያ በቀር ሊከፋፈል የማይችል መሆኑን፣
ሠ)የድርጅቱ አባል ወይም ሠራተኛ በመሆኑ ብቻ በድርጅቱ ንብረት ላይ አንዳችም መብት የማይኖረው መሆኑን፣
ረ) ድርጅቱ ከአባላት የተለየ የራሱ መለያና የሕግ ሰውነት ያለው መሆኑን፣
ሰ) የአባላት መለዋወጥ በድርጅቱ ሕልውና ላይ ተጽዕኖ የሌለው መሆኑን፣
ሸ) አባልነት በውርስ የማይተላለፍ መሆኑን፤
ቀ) የድርጅቱ የሒሳብና የገንዘብ እንቅስቃሴ ተቀባይነት ባለው የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን፣

በ) የድርጅቱን የሥራና የሒሳብ ዕቅድና አፈጻጸም የሚመረምረውና የሚያጸድቀው የበላይ አካል መሆኑን፣
ተ) መተዳደሪያ ደንቡ የሚሻሻልበትን ሥርዓት፣
ቸ) የድርጅቱን የበጀት ዓመት፣
ነ) ድርጅቱ እንዲፈርስ ወይም እንዲዘጋ የሚወስነውን የበላይ አካልና የሚመራበትን ሥርዓት፣
ኘ) ድርጅቱ ሲፈርስ ያለበትን ሕጋዊ ዕዳ ከፍሎ ተራፊው ንብረት የድርጅቱ የበላይ አካል ለመረጠው ሌላ ድርጅት ወይም በኤጀንሲው በኩል በሌላ አካል ወይም በዚህ አዋጅ መሠረት ለተቋቋመው ፈንድ የሚተላለፍ መሆኑን፣
2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ከተዘረዘሩት በተጨማሪ የመተዳደሪያ ደንቡ የሚከተሉትንም ሊያካትት ይችላል:-
ሀ)ለአባልነት ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች፤
ለ) አባልነት የሚቋረጥባቸውን ወይም የሚታገድባቸውን ምክንያቶች፤
ሐ) አባልነት ሲቋረጥ ወይም ሲታገድ በድርጅቱ ውስጥ ይግባኝ የሚጠየቅበት ሥርዓት፣
መ) የአባልነትና ሌሎች ክፍያዎች የሚወሰኑበትና የሚጠየቁበት ሥርዓት፤
ሠ) የሥራ አመራር ኃላፊዎች የሚሾሙበትና የሚሻሩበት ሥርዓት፣ ሥልጣንና ተግባራት፤
ረ) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት የሚሾምበትና የተጠሪነት ሥርዓት፣ ሥልጣንና ተግባራት፤
ሰ) በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ የሚሰማራ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ፤

61. የምዝገባ ውጤት

      በዚህ ሕግ የተመለከቱትን መስፈርቶች አሟልቶ የተመዘገበ ድርጅት፡-
1/ የሕግ ሰውነት ይኖረዋል፤
2/ በሥሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፣ ውል ይዋዋላል፤
3/ ልዩ የሥራ ፈቃድን የሚመለከቱ ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በማናቸውም ሕጋዊ የሥራ መስክ የመሰማራት መብት አለው፤
4/ በሥሙ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የመሆን፣ንብረት የማስተዳደርና የማስተላለፍ መብት አለው። ሆኖም ንብረቱም ሆነ ከንብረቱ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ በስጦታ ለአባላት ጥቅም ወይም ከዓላማው ውጪ ለሆነ ተግባር ሊተላለፍ አይችልም፤
5/  በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ /4/ መሠረት ንብረት ያስተላለፈ ድርጅት በ15 የስራ ቀናት ውሰጥ ለኤጀንሲው ማሳወቅ አለበት ፡፡

62 የሥራ ነፃነት

   1/ ማንኛውም ድርጅት የተቋቋመበትን ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት በየትኛውም ሕጋዊ ሥራ ላይ የመሠማራት ሙሉ መብት አለው።
2/ አገር በቀል ድርጅቶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ለመሥራት፣ እንዲሁም አህጉራዊ፣ ክፍለ አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ዓላማን ተግባራዊ ለማድረግ ይችላሉ።
3/ ማንኛውም ድርጅት፣ በራሱ የፕሮጀክት ሥራን ለመከናወን ወይም ለሌሎች ድርጅቶች የገንዘብና የዕውቀት ድጋፍ ለማድረግ ሊቋቋም ይችላል።
4/ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ጋር ግንኙት ወይም ተያያዥነት ያላቸውን፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች እንዲለወጡ፣ እንዲሻሻሉ ወይም አዲስ ሕጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡ ሐሳብ ማቅረብ ይችላሉ።
5/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ 4 የተመለከተው ቢኖርም በሌላ ህግ ካልተፈቀደላቸው በስተቀር፣ የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ አገር ዜጐች የተመሰረቱ አገር በቀል ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተጽዕኖ መፍጠር፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሰማራት አይችሉም።
6/ የውጭ ድርጅቶች በራሳቸው የፕሮጀክት ሥራዎች ለማከናወን ወይም ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ አገር በቀል ድርጅቶች ጋር የገንዘብ፣ የዓይነትና የዕውቀት ድጋፍ በማድረግ መሥራት ይችላሉ።
7/ የውጭ ድርጅቶች በተቻለ መጠን ከአገር በቀል ድርጅቶች እና መንግስታዊ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት በመሥራት የአገር በቀል ድርጅቶች አቅም እንዲጎለብት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ ።
8/ ማንኛውም ድርጅት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ዘላቂ ልማትን የሚያመጡና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችሉ ወይም የአባላቶቹን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ወይም የተሰማሩበትን የሙያ መስክ ለማሳደግ አስተዋጽዖ ያለው እንዲሆን ተገቢውን ጥረት ማድረግ አለበት።
9/ ለጠቅላላው ሕዝብ ወይም ለሦስተኛ ወገን ጥቅም መሥራትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት፣ የሴቶችን፣ህጻናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአረጋውያንንና ሌሎች ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ወይም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅምን ማካተቱን ማረጋገጥ አለበት።
10/ ማንኛውም ድርጅት ከተመዘገበ በኋላ በሌላ ሕግ የተለየ ፍቃድ እንደሚያስፈልጋቸው በተመለከቱ የሥራ ዓይነቶች ከሚመለከታቸው የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ተገቢውን ፈቃድ ሳያገኝ ወደሥራ መግባት አይችልም።
11/ የማንኛውም ድርጅት አባል፣ አመራርና ሠራተኞች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የድርጅቱን ጥቅም የማስቀደምና ከእነሱ ጥቅም ጋርም እንዳይጋጭ ተገቢውን ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

63 የሀብት አሰባሰብ እና አስተዳደር

1/ ማናቸውም ድርጅት፡-

     ሀ) ለሚተገብረው ፕሮጀክት ዘላቂነት አስፈላጊ በመሆናቸው፣ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ፕሮጀክቱ ከሚፈጸምበት ቦታ እንዳይወጡ በፕሮጀክት ስምምነቱ ላይ በግልጽ ከተመለከቱ ንብረቶች በስተቀር፣ ማንኛውም ድርጅት ንብረቱን ከአንድ ክልል ወደሌላ ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የማንቀሳቀስ ሙሉ መብት አለው።
    ለ) ለዓላማው መሳካት ገቢ ለማግኘት በማንኛውም ሕጋዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ አግባብነት ባላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ሕጎች መሠረት የመሳተፍ መብት አለው። ሆኖም ከሥራው የሚገኘውን ትርፍ ለአባላት ጥቅም ማስተላለፍ አይችልም።
   ሐ) ለዓላማው መሳካት ከየትኛውም ሕጋዊ ምንጭ ገንዘብ የመጠየቅ፣ የመቀበልና የመጠቀም መብት አለው።
2/ ለጠቅላላው ሕዝብ ወይም ለሦስተኛ ወገን ጥቅም መሥራትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት፣ የአስተዳደር ወጪው ከገቢው ከ20 በመቶ ሊበልጥ አይችልም። ለዚህ ድንጋጌ አፈጻጸም ‹‹የአስተዳደር ወጪ›› ማለት ድርጅቱ ከሚያከናውነው የፕሮጀክት ሥራ ጋር ተያያዥነት የሌለው፣ነገር ግን ለድርጅቱ ሕልውና ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነ እና ከአስተዳደር ሥራዎች ጋር የተያያዘ ወጪ ሲሆን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅሞችን፣ ከአስተዳደር ሥራ ጋር የተያያዘ የአላቂና ቋሚ እቃዎች ግዢን፣ የጥገናና እድሳት ወጪዎችን፣የቢሮ ኪራይ፣የፓርኪንግ ክፍያዎች፣ የኦዲት አገልግሎት፣ የማስታወቂያ ክፍያ፣ የባንክ አገልግሎት፣የመብራት፣የስልክ፣ የፋክስ፣ የውሃ፣ኢንተርኔት፣ የፖስታና የሕትመት አገልግሎት ወጪዎችን፣ታክስ፣ ለአስተዳደር ሥራ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ግዢ፤ ጥገና፤ የነዳጅና ዘይት እንዲሁም የመድኅን ግዢ ወጪዎችን፣ የቅጣት ክፍያዎችን፣ እንዲሁም የጥብቅና አገልግሎት ክፍያን ያካትታል።

3/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተው ድንጋጌ በልዩ ሁኔታ ተፈጻሚ የማይሆንባቸውን ድርጅቶች በሚመለከት ኤጀንሲው መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

64፡ በገቢ ማስገኛ ስራዎች ስለመሠማራት

1. ከላይ በአንቀጽ 63 (1)(ለ) መሠረት በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ የሚሰማራ ድርጅት፣ አግባብነት ባላቸው የንግድ ፈቃድና ምዝገባ ህጎች መሠረት፣ አዲስ የንግድ ድርጅቶችን (ኩባንያዎችን) በማቋቋም፣ በነባር የንግድ ድርጅቶች ውስጥ አክሲዮን በመያዝ፣ ወይም የንግድ ስራን በብቸኛ ባለቤትነት በማካሔድ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ማከናወን ይችላል፡፡
2. ድርጅቱ በራሱ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በሚያከናወንበት ጊዜ ለዚሁ ስራ የተለየ የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ እንዲሁም በንግድ እና ታክስ ህጉ በሚጠየቀው መሠረት የገቢ ማስገኛ ስራውን የሚመለከት የተለየ የሂሳብ መዝገብ መያዝ ይኖርበታል፡፡
3. አግባብነት ያላቸው የታክስ፣ የንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ እንዲሁም የአንቨስትመንት ሕጎች በገቢ ማስገኛ ስራዎችን በመሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
4. ድርጅቱ ከገቢ ማስገኛ ስራው የሚያገኘው ገቢ፣ የድርጅቱን የአስተዳደር እና የፕሮገራም ወጪዎች ለመሸፈን ይውላል፡፡
5. ድርጅቱ ከገቢ ማስገኛ ስራው የሚያገኘው ገቢና ሃብት ለአባላት እንዲሁም ለሠራተኞች ሊከፋፈል አይችልም።
6. በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ /1/ መሠረት ድርጅቶች ህዝባዊ መዋጮ ሲሰበስቡ ለኤጀንሲው ማሳወቅ አለባቸው ፡፡
7.  በዚህ አንቀፅ መሠረት በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ለኤጀንሲው በአስራ አምስት የስራ ቀናት ማሳወቅ አለበት ፡፡

65. በሥራ መሪነት ወይም በቦርድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መሥራት የማይችሉ  ሰዎች

    1/ ማንኛውም ሰው በአንድ ድርጅት ውስጥ በሥራ መሪነት ወይም በድርጅቱ የቦርድ/ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መሥራት የማይችለው:-
    ሀ) በማታለል ወይም ታማኝነትን በማጓደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተቀጣና ያልተሰየመ ከሆነ፤
     ለ) በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የሲቪል መብቱን የተገፈፈና መብቶቹ ያልተመለሱለት ከሆነ፣
    ሐ) በሕግ መሠረት ከችሎታ ማጣት የተነሳ መሥራት የማይችል ከሆነ፣
   መ) በፍርድ ቤት ክልከላ የተደረገበት ከሆነ ነው።
2/  ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የማናቸውም ድርጅት የቦርድ ወይም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆነ ሰው በዚያው ድርጅት ውስጥ የሥራ መሪ ወይም ተቀጣሪ ሠራተኛ ሆኖ መሥራት አይችልም።
3/ የድርጅቱ የምዝገባ ማመልከቻ የዚህን አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) የሚጥስ የቀረበ ከሆነ ኤጀንሲው ድርጅቱን አይመዘግብም።

66. የድርጅቶች መዝገብ

    1/ ኤጀንሲው ድርጅቶች የሚመዘገቡበት መዝገብ ይይዛል።
    2/በኤጀንሲው ትክክለኛ ቅጂ ስለመሆኑ የተረጋገጠ የመዝገቡ ሙሉ ወይም ከፊል ግልባጭ በማናቸውም የክርክር ሂደቶች በማስረጃነት ተቀባይነት ይኖረዋል።
    3/ ኤጀንሲው በዚህ አዋጅ መሠረት የተመዘገቡትን እንዲሁም የታገዱትንና ከመዝገብ የተሠረዙትን ድርጅቶች ዝርዝር በየስድስት ወሩ በጋዜጣ ያወጣል።

67. የድርጅት ቅርንጫፍ

   1/ ማንኛውም ድርጅት አስቀድሞ ለኤጀንሲው በማሳወቅ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ቅርንጫፍ ሊከፍት ይችላል።

   2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት ለሚከፈት ቅርንጫፍ የሚሰጠው ሥልጣን ራሱን የቻለ ድርጅት የሚያደርገው ወይም ዋናው መስሪያ ቤት በቂ ቁጥጥር እንዳያደርግበት የሚከለክል ሊሆን አይችልም።

68. ለውጥን ስለማሳወቅ

   1/ ማንኛውም ድርጅት በሚከተሉት ጉዳዬች ላይ ለውጥ ሲያደርግ ለኤጀንሲው ማሳወቅና ማስመዝገብ አለበት፡
ሀ)የሥያሜ ወይም የምልክት ለውጥ፣
ለ) የሥራ ዘርፍ ለውጥ፣
ሐ) የዋና መሥሪያ ቤት አድራሻ ለውጥ፣
መ) የሥራ ክልል ለውጥ፣
ሠ) የሥራ አመራር አባላት ወይም የሥራ መሪ ለውጥ፣
ረ) በመተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚደረግ ማናቸውም ለውጥ፣
ሰ) የባንክ ሒሳብና ፈራሚዎች ለውጥ፣
   2/ በዚህ አንቀጽ መሠረት የተደረገ ለውጥ የድርጅቱን ማናቸውም መብቶች ወይም ግዴታዎች አይነካም።69. የምስክር ወረቀትን በይፋ ስለማሳየት
ማንኛውም ድርጅት የምዝገባ ምስክር ወረቀቱን በዋናው መስሪያ ቤት፣ እንዲሁም ግልባጩን በየቅርንጫፎቹ ለማናቸውም ጎብኚ ሊታይ በሚችል ቦታ ማስቀመጥ ይኖርበታል። በተጨማሪም የድርጅቱ ሥምና መለያ ምልክት በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለሕዝብ ሊታይ በሚችል ግልጽ ስፍራ መቀመጥ ይኖርበታል።

7ዐ. ሕልውናን ስለማረጋገጥ

   1/ ማንኛውም ድርጅት በዚህ አዋጅ ውስጥ ሪፖርት ለማቅረብ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ባለፈ በሦስት ወራት ውስጥ ሪፖርት ካላቀረበ ኤጀንሲው የድርጅቱን ሕልውና ለማረጋገጥ በጋዜጣ ጥሪ ያደርጋል።
   2/ ከላይ የተመለከተው ጥሪ በጋዜጣ በወጣ በ30 ቀናት ውስጥ ድርጅቱ በርግጥም ሕልውና
          ያለው ከሆነ የድርጅቱ ሕጋዊ ተወካይ ቀርቦ በዚህ ሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለኤጀንሲው ሪፖርት ያላቀረበበትን ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅበታል። ተወካዩ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቀርቦ ድርጅቱ ሪፖርት ያላደረገበትን በቂ ምክንያት ካላቀረበ ዋና ዳይሬክተሩ ጉዳዩን ለቦርዱ አቅርቦ ድርጅቱ እንዲፈርስ ያስወስናል።

ክፍል አራት
ሒሳብና ሪፖርት

71. የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ

    1/ ማናቸውም ድርጅት የድርጅቱን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ተቀባይነት ባለው የሒሳብ አሰራር የተዘጋጀ የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ አለበት።
    2/ የሒሳብ ሰነዶቹ የድርጅቱን ገቢና ያወጣውን ወጪ፣ የወጪውን ምክንያት፣ ሐብትና ዕዳ፣ የለጋሾችን ማንነትና የገቢውን ምንጭ ያካተቱ መሆን አለባቸው።
   3/ ድርጅቱ የሥራ መሪዎች በዚህ አንቀጽ መሠረት የተዘጋጁ የሒሳብ ሰነዶችን፣ የሒሳብ ዓመቱ ካለቀ በኋላ ቢያንስ ለአምስት ዓመት ጠብቀው የማቆየት ግዴታ አለባቸው።

72. ዓመታዊ የሒሳብ መግለጫና ምርመራ

    1/ ማንኛውም ድርጅት ተቀባይነት ባላቸው መመዘኛዎች መሠረት የተዘጋጀ ዓመታዊ የሒሳብ መግለጫ ለኤጀንሲው በአድራሻው መላክ አለበት።
    2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም፣ በበጀት አመቱ ከሁለት መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ገቢን፣ ወጪን፣ ሐብትና ዕዳን የሚያመለክት መግለጫ ብቻ ማቅረብ ይችላል።
   3/ ከላይ በንዑስ ቁጥር 2 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የማንኛውም ድርጅት ሒሳብ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በ 3 ወራት ውስጥ በተመሰከረለት ኦዲተር መመርመር አለበት።
   4/ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የድርጅቱ አባላት ወይም ለጋሽ ድርጅቶች ወይም ከድርጅቱ ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ያላቸው መንግስታዊ አካላት የሒሳብ ምርመራ እንዲደረግ ከጠየቁ ኤጀንሲው የድርጅቱ ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ሊያዝ ይችላል።

   5/ የድርጅቱ ሒሳብ የበጀት ዓመቱ ባለቀ በአምስት ወራት ውስጥ ካልተመረመረ እና ይህንን ለመፈጸም ድርጀቱ ፈቃደኛ ካልሆነ ኤጀንሲው የውጭ ኦዲተር ሾሞ ማስመርመር ይችላል።
   6/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 መሠረት በኤጀንሲው በተሾመው ኦዲተር ለተከናወኑ ማናቸውም የኦዲት ሥራዎች ወጪ የሚከፍለው የሚመለከተው ድርጅት ወይም ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የሥራ መሪዎቹ ይሆናሉ።

73. ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት

   1/ የሥራ መሪዎች የድርጅቱን የእያንዳንዱን የበጀት ዓመት ዋና ዋና ክንዋኔዎች የሚያሳይ ሪፖርት የሒሳብ ዓመቱ ባለቀ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለኤጀንሲው ማቅረብ አለባቸው።
   2/ ማንኛውም የሥራ ክንውን ሪፖርት ለኤጀንሲው ሲቀርብ የሒሳብ መግለጫ አብሮ መያያዝ አለበት።
   3/ ኤጀንሲው የቀረበለትን ሪፖርት በመመርመር ድርጅቱ ተጨማሪ ማስረጃ ወይም ማብራሪያ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል።


74. ዓመታዊ ሪፖርት ለሕዝብ ክፍት ስለማድረግ

   1/ በኤጀንሲው ዘንድ የሚገኝ ማናቸውም የድርጅት ዓመታዊ ሪፖርት ወይም ሌላ ሰነድ ጉዳዩ በሚመለከተው አካል ወይም በድርጅቱ አባላት ሲጠየቅ በማናቸውም አመቺ ጊዜ ክፍት መደረግ አለበት።
   2/ ማናቸውም ድርጅት ዓመታዊ የሥራ ክንውን እና የኦዲት ሪፖርቱን ለአባላቱና ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ አለበት።

75. የባንክ ሒሳብ ስለመክፈት

   1/ ማንኛውም ድርጅት የባንክ ሒሳብ ለመክፈት በቅድሚያ ከኤጀንሲው በጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት አለበት። ኤጀንሲው የባንክ ሒሳብ ለመክፈት ጥያቄ በቀረበለት በ5 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል።
   2/ የማንኛውም ድርጅት የገንዘብ እንቅስቃሴ በስሙ በተከፈተ የባንክ ሒሳብ መከናወን ይኖርበታል።
   3/ ማንኛውም ባንክ ኤጀንሲው በጠየቀ ጊዜ ወዲያውኑ በማናቸውም የድርጅት ሥም የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦችን ዝርዝርና የሒሳብ መግለጫዎችን የመስጠት ግዴታ አለበት።
   4/ የድርጅት የባንክ ሒሳብ መንቀሳቀስ የሚችለው፣ በመተዳደሪያ ደንቡ በተመለከተው አኳኋን ነው።76. የውጭ ዜጎችን ስለመቅጠር

    1/ ማንኛውም ድርጅት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሥራ ፈቃድ ያልተሰጠውን የውጭ ዜጋ መቅጠር አይችልም።
   2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ ቢኖርም የውጭ ድርጅት የውጭ አገር ዜጋን የአገር   ውስጥ ተወካይ አድርጎ ለመመደብ ገደብ አይኖርበትም።
   3/ ከአገር ውስጥ ተወካዩ በስተቀር ሌሎች የውጭ አገር ዜጎች በድርጅቱ ሊቀጠሩ የሚችሉት ሥራው በኢትዮጵያውያን ሊከናወን የማይችል ስለመሆኑ በሥራ ፈቃድ ሰጪው መሥሪያ ቤት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።
   4/ በድርጅቱ መደበኛ ደመወዝ ሳይከፈላቸው በሙያቸው በበጎ ፈቃደኝነት ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ለማገልገል የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችን በሚመለከት የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ተፈጻሚ አይሆንም።

ክፍል አምስት
ሕግን ስለማስከበር

77. ምርመራ የማድረግ ሥልጣን

    1/ ከመንግሥት አካላት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች ወይም ከሕዝብ ከሚቀርቡ ጥቆማዎች ወይም ኤጀንሲው ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት ከሚገኙ መረጃዎች በመነሳት ማናቸውም ድርጅት ሥራውን በሕግ መሠረት እየሰራ ስለመሆኑ ኤጀንሲው ምርመራ ሊያደርግ ይችላል።
   2/ ከላይ የተጠቀሰው ቢኖርም ኤጀንሲው ምርመራ ለማድረግ ሲወስን ምርመራውን ለማከናወን በቂ ምክንያት መኖሩን በቅድሚያ ማረጋገጥ አለበት።

   3/ የምርመራ ሥራዎች በተቻለ ፍጥነት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁና የድርጅቱን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና ሕልውና አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ኤጀንሲው ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አለበት።
   4/ ኤጀንሲው የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት፣ ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥና በዚህ ምክንያትም የድርጅቱ እንቅስቃሴ ማገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ከሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ የዕገዳ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል። ሆኖም ቦርዱ በሶስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ እገዳው ቀሪ ይሆናል ፡፡
   5/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት ዋና ዳይሬክተሩ በሰጠው እግድ ላይ ድርጅቱ በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለቦርዱ ማቅረብ የሚችል ሲሆን፣ በቦርዱ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ድርጅቱ ውሳኔው  ተሰጠበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ማቅረብ ይችላል።

78. አስተዳደራዊ እርምጃ ስለመውሰድ

   1/  ይህን አዋጅ እና ሌሎች ሕጎችን ለሚጥሱ ድርጅቶች ኤጀንሲው ማስጠንቀቂያ ሊሰጥ ይችላል።
   2/ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በፅሑፍ ሆኖ፣ የተፈጸመውን የሕግ ጥሰት፣ ሊደረግ የሚገባውን ማስተካከያ እና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መስተካከል እንዳለበት በግልጽ ማሳየት አለበት። ኤጀንሲው ለማስተካከያ የሚሰጠው ጊዜ የተፈጸመውን ጉድለት ወይም ጥፋት ክብደትና የጉዳዩን ውስብስብነት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።
   3/ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ማስተካከያ የማያደርግ ከሆነ ወይም ድርጅቱ የፈጸመው ጥፋት ከባድ መሆኑን ኤጀንሲው ሲያምንበት ለድርጅቱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል።
   4/ በተሰጠው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሠረት ድርጅቱ አሰራሩን የማያስተካክል ከሆነ ድርጀቱ እንዲታገድ ዋና ዳይሬክተሩ ሊወስን ይችላል። የዋና ዳይሬክተሩ ውሳኔ በቦርዱ ካልተነሳ ወይም በፍርድ ቤት ካልታገደ በቀር፣ የዕገዳ ውሳኔው በተሰጠ በሦስት ወራት ውስጥ ማስተካከያ ያላደረገ ድርጅት እንዲፈርስ ቦርዱ ይወስናል።
   5/ በቦርዱ የመፍረስ ውሳኔ የተሰጠበት ድርጅት አባላት፣ መሥራቾች ወይም ኃላፊዎች ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ።

   6/ በድርጅቱ የተፈጸመው ሕግ የመተላለፍ ተግባር በወንጀል የሚያስጠይቅ ሲሆን ኤጀንሲው ጉዳዩን ሥልጣን ላለው የፖሊስ ወይም የዐቃቤ ሕግ ተቋም ይመራል።

79. የመሰማት መብት

ኤጀንሲው በማንኛውም ድርጅት ላይ የትኛውንም ዓይነት አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ድርጅቱ መከራከሪያዎቹንና ማስረጃዎቹን የማቅረብና የመሰማት መብት አለው።

ክፍል ስድስት
ስለ ድርጅቶች መዋሐድ፣መከፋፈል እና መለወጥ

8ዐ. መዋሐድ

   1/ ቁጥራቸው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ድርጅቶች አግባብነት ባላቸው ሕጎችና በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት በአዲስ ስም ወይም ከሚዋሐዱት ድርጅቶች በአንዱ ስም ሊዋሐዱ ይችላሉ።
   2/ ውሕደቱ ሲፈጸም የቀድሞዎቹ ድርጅቶች መብትና ግዴታዎች እንዲሁም በውስጣቸው የነበሩ ሠራተኞች እንደ አግባብነታቸው በውህደት ወደተፈጠረው ድርጅት ይተላለፋሉ።
   3/ በውሕደቱ የተፈጠረው አዲስ ድርጅት በዚህ አዋጅ መሠረት መመዝገብ አለበት።

81. መከፋፈል

  1/ አንድ ድርጅት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በተመለከተው መሠረት በድርጅቱ የበላይ አካል ውሳኔ ሊከፋፈል ይችላል።
  2/ በመከፋፈሉ ውሳኔ ላይ በሌላ ሁኔታ ካልተመለከተ በቀር፣ በክፍፍሉ የተፈጠረው እያንዳንዱ    ድርጅት የቀድሞው ድርጅት ላለበት ግዴታና መብት እኩል ተካፋይ ነው።
  3/ የቀድሞው ድርጅት ህልውና የሚያበቃው ለአዲሶቹ ድርጅቶች የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሲሰጥ ነው።
  4/ በአዲሶቹ ድርጅቶች ሙሉ ስምምነት ከነሱ አንዱ የቀድሞውን ድርጅት ስም ይዞ ሊቆይ ይችላል።


82. መለወጥ

   1/ አንድ ድርጅት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በተመለከተው መሠረት በድርጅቱ የበላይ አካል ውሳኔ ወደሌላ ዓይነት ድርጅት ሊለወጥ ይችላል።
   2/ ለውጡ ሲፈጸም የቀድሞው ድርጅት መብትና ግዴታዎች እንዲሁም በውስጣቸው የነበሩ ሠራተኞች እንደአግባብነታቸው ወደተለወጠው ድርጅት ይተላለፋሉ።
   3/ የተለወጠው አዲስ ድርጅት በዚህ አዋጅ መሠረት እንደገና መመዝገብ አለበት።

ክፍል ሰባት
ስለድርጅቶች መፍረስ

83. የድርጅቶች መፍረስ

   1/ አንድ ድርጅት የሚፈርሰው፡
ሀ) በመተዳደሪያ ደንቡ ሥልጣን ባለው አካል እንዲፈርስ ሲወሰን፣
ለ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7ዐ ወይም 78(4) መሠረት ድርጅቱ እንዲፈርስ በኤጀንሲው ቦርድ ሲወሰን፤ወይም
ሐ) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ነው።
   2/ ፍርድ ቤት አንድ ድርጅት እንዲፈርስ የሚወስነው፡-
ሀ) ድርጅቱ በከባድ የወንጀል ድርጊት ወይም በተደጋጋሚ በቀላል ወንጀል በመሳተፍ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ፣ ወይም
ለ) ዕዳውን የመክፈል ችሎታ የሌለው ሲሆን ብቻ ነው።
   3/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) /ሀ/ መሠረት በአባላት ውሳኔ የፈረሰ ድርጅት ውሳኔውን ለኤጀንሲው በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።
   4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ መሠረት ድርጅቱ ለኤጀንሲው የሚያቀርበው ማስታወቂያ፣ ድርጅቱ እንዲፈርስ የተወሰነበትን ቃለ ጉባኤ፣ የድርጅቱን ወቅታዊ የሥራ ክንውንና የሒሳብ መግለጫ አያይዞ ማቅረብ አለበት።

84. የመፍረስ ውጤት

    1/ በአንቀጽ 83 መሠረት ድርጅቱ እንዲፈርስ ሲወሰን ንብረቱ ወዲያውኑ በኤጀንሲው በሚሾም ሒሳብ አጣሪ ኃላፊነት ሥር ይሆናል።
    2/ ሒሳብ አጣሪው፣ ከድርጅቱ ዓላማ ጋር የተያያዙና ሊቋረጡ የማይችሉ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ካልሆነ በስተቀር ከሒሳብ ማጣራት ውጪ ሌላ ተግባር ማከናወን አይችልም።

   3/ የድርጅቱን ዕዳዎችና የማፍረስ ሂደቱን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ወጪዎች ተጠናቀው ከተከፈሉ በኋላ ሒሳብ አጣሪው የድርጅቱ ቀሪ ገንዘብ ወይም ንብረት በድርጅቱ የመተዳደሪያ ደንብ ወይም በድርጅቱ የበላይ አካል አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ለሌላ ድርጅት እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡
   4/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረትበድርጅቱ የመተዳደሪያ ደንብ ወይም በድርጅቱ የበላይ አካል ውሳኔ ላይ ካልተመለከተ ቀሪ ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ኤጀንሲው በሚወስነው መሠረት ለሌላ ድርጅት እንዲተላለፍ ይደረጋል።
   5/ የድርጅቱ የሒሳብ ማጣራት ሥራዎች ሲጠናቀቁ፤በሒሳብ አጣሪው ጠያቂነት ኤጀንሲው ድርጅቱን ከመዝገብ ይሰርዛል።
     6/  የዚህ አንቀፅ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ህብረቶች ወይም የህብረቶች ህብረት በሚፈርሱበት ጊዜ ቀሪ ንብረቶች ወደ አባል ድርጅቶች ወይም ህብረቶች ሊተላለፉ ይችላሉ ፡፡

ክፍል ስምንት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

85. የድርጅቶች ምክር ቤት

1/ በሁሉም ድርጅቶች ሙሉ ተሳትፎ የሚመራ ምክር ቤት በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
2/ ኤጀንሲው የምክር ቤቱን መሥራች ጉባዔ ይጠራል፣ ያስተባብራል።
3/ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ አደረጃጀቶች ይኖሩታል። ምክር ቤቱ የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ያወጣል።
    4/ የድርጅቶች በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ የሚወከሉበት ስርዓት በምክር ቤቱ መመሪያ ይወሰናል።
    5/ ምክር ቤቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-
ሀ) ከኤጀንሲው፣ ከለጋሾችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ዘርፉ
     ሊከተለው የሚገባውን የስነምግባር ደንብና ማስፈጸሚያ ስልት ያወጣል፣ አተገባበሩን በቅርበት ይከታተላል፣
ለ) በድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር ላይ ለኤጀንሲውና ለቦርዱ ምክረ-ሃሳብ ያቀርባል፣
           ሐ) ዘርፉን ይወክላል፣ ያስተባብራል፣

    6/ ምክር ቤቱ በኤጀንሲው ቦርድ ውስጥ ድርጅቶችን የሚወክሉ 3 ተወካዮችን ይመርጣል።
    7/ የምክር ቤቱ በጀት ከአባላት መዋጮና ከሌሎች ሕጋዊ ምንጮች ይሆናል።
    8/ ለምክር ቤቱ መመሥረትና መጠናከር ኤጀንሲው አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ያደርጋል።

86. የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ

1/ በኤጀንሲው የሚተዳደር የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
2/ የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ በጎ ፈቃደኝነትን እና የዘርፉን ዕድገት ለማበረታታት፣
     በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያገለግሉ ድርጅቶችን ለማበረታት ይውላል።
3/ የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ ገቢውን የሚያገኘው፦
ሀ) ከዚህ አዋጅ በፊት ከፈረሱ ማኅበራትና ድርጅቶች የተገኘ በኤጀንሲው ይዞታ የሚገኝ   ንብረት፣
ለ) በኤጀንሲው ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ከሚፈርሱ ድርጅቶች የሚገኝ ንብረት፣
ሐ) በመንግሥት ለፈንዱ የሚደረግ ድጎማ፣
4/ ድርጅቶች ለሲቪል ማኅበረሰብ ፈንዱ መዋጮ ማድረግ አይችሉም።
5/ የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ አስተዳደርን በተመለከተ ኤጀንሲው ዝርዝር መመሪያ ያወጣል።

87. የተሻሩ እና ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ሕጎች

1/ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001፣ የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ (አዋጅ ቁ.   166/1952) አንቀጽ 25፣ በዚህ አዋጅ ተሽረዋል።
2/ በዚህ አዋጅ ከተደነገጉ ጉዳዮች ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ልማድ ወይም አሰራር በዚህ አዋጅ በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

88. የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች

1. የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001፣ እንዲሁም ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ያወጣቸው መመሪያዎች ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ተፈፃሚ ይሆናሉ።
2. በአዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት የተገኙ መብቶችና ግዴታዎች በዚህ አዋጅ የተመለከቱትን መሠረታዊውን መብቶችና ግዴታዎች እስካልተቃረኑ ድረስ ባሉበት ይቀጥላሉ።
3. በአንድ ክልል ውስጥ ብቻ ለመሥራት ከሚመዘገቡ ድርጅቶች በስተቀር፣ በአዋጅ ቁጥር
   621/2001 መሠረት የተመዘገቡ ድርጅቶች ይህ አዋጅ ከጸናበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና በኤጀንሲው መመዝገብ አለባቸው።
4. በአንድ ክልል ውስጥ ብቻ የሚሰሩ ድርጅቶች አግባብነት ባለው የክልሉ መዝጋቢ አካል ይመዘገባሉ።
5. በአዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት
     ኤጀንሲ ስልጣንና ተግባራት እንዲሁም መብትና ግዴታዎች በዚህ አዋጅ እንደተሻሻሉ ወደ ኤጀንሲው ይተላለፋሉ።

89. ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣን

   1/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል።
   2/ ኤጀንሲው ይህንን አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የሚወጣውን ደንብ ለማስፈፀም መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

90. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል።

አዲስ አበባ  ____ቀን 2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment