Tuesday, August 25, 2020

አሠሪና ሠራተኛ ህግ- በሠራተኛ ላይ የሚወሰድ የዲሲፕሊን ቅጣት ህጋዊነት --ሰ/መ/ቁ. 37391

 

የሰ/መ/ቁ. 37391

የካቲት 3 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

       ሐጐስ ወልዱ

       ታፈሰ ይርጋ

       በላቸው አንሺሶ

       ሱልጣን አባተማም

አመልካች፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ - ጠበቃ ንጉሴ ገዛኸኝ ቀረበ

ተጠሪዎች፡- 1. ስዩም ማሞ ቀረበ

           2. በየነ አበራ ቀረበ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 377/96 መሰረት በአሰሪና ሰራተኞች መካከል የተደረገውን ክርክር የሚመለከት ነው፡፡ ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነው፡፡ ከሣሾች የነበሩት የአሁኖቹ ተጠሪዎች ናቸው፡፡ በአመልካች ላይ ክስ የመሰረቱት ጥፋት ሳንፈጽም የገንዘብ ቅጣት/ከደመወዛችን ላይ እየተቀነሰ/ እንድንከፍል ተወስኖብናል፡፡ ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ቅጣቱና ማስጠንቀቂያው ይሰረዝልን ዘንድ ይወሰንልን በማለት ነው፡፡ አመልካች ደግሞ ለክሱ በሰጠው መልስ ከሣሾች ግንቦት 6 ቀን 99 ዓ.ም በማታው ፈረቃ የነበረውን የስራ ጫና ለማደላደል አለቃ በሚወስነው የአሰራር አፈጻጻም ስርአት መሰረት ከነበሩበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ እንዲሰሩ አመራር ቢሰጣቸው አመራሩ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ነው ቅጣቱ የተወሰነባቸው፡፡ ቅጣቱ የተወሰነው በሕብረት ስምምነቱ መሰረት በመሆኑ ሕጋዊ ነው፡፡ የሚሰረዝበት የሕግ ምክንያት የለም በማለት ስለመከራከሩ ኀዳር 2 ቀን 2000 ዓ.ም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ የስራ ክርክር ችሎት ከፃፈው የመልስ ማመልከቻ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በዚህ መልክ ክርክር የቀረበለት የስራ ክርክር ችሎትም ክርክሩን ከመረመረ በኋላ፣ በከሣሾች ላይ ቅጣቱ የተወሰነው በማታ ሽፍት አንሰራም ብለዋል በሚል እንጂ ከነበሩበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረን አንሰራም ብለዋል በሚል አይደለም የሚል ምክንያት በመስጠት በአመልካች የተሰጠ ነው ቅጣት እንዲሰረዝ ወስኖአል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የስራ ክርክር ችሎትም ውሳኔው ጉድለት የለበትም ብሎአል፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበውን በዚሁ ላይ ነው፡፡

      በበኩላችንም አመልካች ሚያዝያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፈው ማመልከቻ ያቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ ተጠሪዎችን አስቀርበን ክርክሩን ሰምተናል፡፡ አቤቱታው በሰበር ችሎት እንዲታይ የተወሰነው በአመልካች ተሰጥቶ የነበረውን የቅጣት ውሳኔ በፍ/ቤቶቹ በተሰጠው ውሳኔ የተሰረዘበትን አግባብ ለመመርመር ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ነጥብ ከግራ ቀኝ ወገኖች ክርክር፣አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና ከሕጉ ጋር አገናዝበን መርምረናል፡፡

      ቀደም ሲል እንደተገለጸው ተጠሪዎች ቅጣት የተወሰነባቸው በአለቃቸው የተሰጣቸውን የስራ መመሪያ ለመቀበል ፍቃደኛ ሆነው አልተገኙም በሚል ነው፡፡ መስከረም 8 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፉት የክስ ማመልከቻ እንደሚታየው በአለቃቸው የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመቀበል በስራ ቦታው እንደተገኙ ገለጸዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ለቅጣቱ መነሻ ሆኖአል የተባለው ጥፋት /የአለቃ መመሪያ አለመቀበል/ አለመፈጸማቸው በመግለጽ መከራከራቸውን ነው፡፡ አመልካችም ኀዳር 2 ቀን 2000 ዓ.ም በፃፈው መልስ የበኩሉን የመከላከያ ክርክር ያቀረበ ሲሆን፣ይዘቱም ከላይ የተመለከተው ነው፡፡ እንግዲህ ከግራ ቀኝ ወገኖች የቀረበው የጽሑፍ ክርክር በግልጽ እንደሚያመለክተው አከራካሪው ጭብጥ ቁልጭ ብሎ መውጣቱን ነው፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 247/1/ እንደተደነገገው የነገር ጭብጥ የሚመሰረተው አንደኛው ተከራካሪ ወገን ያመነውን የሕግ ወይም የፍሬ ነገር አግባብ ሌላው ተከራካሪ ወገን በማስተባበል የካደ እንደሆነ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ በአመልካች ለቅጣቱ መወሰን መሰረት ሆኖአል ያለው የፍሬ ነገር አግባብ በተጠሪዎቹ ተክዶአል፡፡ በመሆኑም ይህ የፍሬ ነገር ጭብጥ እንደየሁኔታው ግራ ቀኝ ወገኖች ከሚያቀርቡት ማስረጃ አንፃር ታይቶ የሚነጥር ነው፡፡ በመቀጠልም በፍሬ ነገር ረገድ የተረጋገጠ እውነታ ካለ አግባብ ካለው ሕግ አንፃር በመመርመር አግባብ ወዳለው ውሳኔ መድረስ ይችላል፡፡

      አቤቱታ በቀረበበት ውሳኔ እንደሚታየው ክርክሩ ከፍ ሲል በተመለከተው አኳኋን አልተመራም፡፡ የክርክሩ አመራር የክርክር አመራር ስርአት ወይም አግባብ ተከትሎ ካልተከናወነ ፍትሐዊ ውሳኔ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ አንድን ክርክር በመምራት ላይ ያለ ፍ/ቤት ሊያከናውናቸው ከሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛው የክርክሩን ጭብጥ ለይቶ ማውጣት ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ በስር ፍ/ቤቶች ሳይከናወን የቀረውም ይኸው ተግባር ነው፡፡ ትክክለኛው ጭብጥ ባለመያዙም የደረሰበት ድምዳሜ ትክክል ነው ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ችለናል፡፡

ው ሳ ኔ

1.   የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 37409 ጥር 28 ቀን 2000 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 37391 መጋቢት 22 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348/1/ መሰረት ተሽረዋል፡፡

2.   የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተጠሪዎች ላይ ለተወሰነው ቅጣት መሰረት ሆኖአል የተባለውን ጥፋት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም የሚለውን የፍሬ ነገር ጭብጥ በግራ ቀኝ ወገኖች በሚቀርብለት ማስረጃ መሰረት እንዲያነጥር /እንዲያረጋግጥ/፤ በመቀጠልም በፍሬ ነገር ረገድ አጣርቶ የደረሰበትን ድምዳሜ አግባብ ካለው ሕግ ጋር አገናዝቦ ከመረመረ በኋላ የመሰለውን ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ ጉዳዩ ይመለስለት ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡

3.   በዚህ ሰበር ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት ያወጣውን ወጪና ኪሣራ በተመለከተ ግራ ቀኝ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ይመለስ፡፡

ት እ ዛ ዝ

      ከፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ የመጣው ቁ. 37409 የሆነው መዝገብ ወደ መጣበት ይመለስ፡፡፡

                                    የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃ

No comments:

Post a Comment