Wednesday, August 26, 2020

አሠሪና ሠራተኛ ህግ--የኤጀንሲ ሠራተኞች (Agency Employment)-ሰበር መ/ቁ 38435

 የሰበር መ/ቁ 38435

 የካቲት17 ቀን 2001 ዓ.ም

     ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

             ሐጎስ ወልዱ

             ሒሩት መለሠ

             በላቸው አንሺሶ

             ሡልጣን አባተማም

አመልካች፡- ኤስ ኦ-ኤስ የህፃናት መንደር ጠበቃ አቶ አይሸሽም መድፍ ቀረሱ፡፡


ተጠሪዎች፡-1. አቶ ከበደ ኩምሳ

          2. አቶ ሚደቅሳ ተክሌ

          3. አቶ ወልደጊዮርጊስ ሙለታ  

          4. አቶ ፋሲል ገ/ሕይወት       ቀረቡ

          5. አቶ አበራ ታፈሰ

          6. አቶ ጌታሁን በላቸው

                 መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

                        ፍ ር ድ

      ለጉዳዩ መነሻ የሆነው ክርክር የተጀመረው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነው የአሁኑ ተጠሪዎች ከሳሾች ሲሆኑ አመልካች ተከሣሽ ነበር፡፡ ከሳሾች ያቀረቡት ክስ በድርጅቱ በጥበቃ ሠራተኛነት ለበርካታ ስናገለግል የቆየን ሲሆን ስራውን በሌላ ድርጅት ላሠራ ወስኛለሁ በሚል ሰበብ ያለአግባብ ከስራ ውጪ የሥራ ውላችንን ያቋረጠ በመሆኑ ወደ ሥራችን እንድንመለስ የማይመልሰን ከሆነ ካሳና ጥቅማጥቅም እንዲከፈል ይወሰንልን የሚል ነው፡፡

      አመልካችም መጋቢት 5 ቀን 1999 ዓ.ም  ጽፎ ባቀረበው መልሱ የድርጅቱን አሰራር ለማሻሻል ከሳሾች ይሠሩበት የነበረውን የጥበቃ ሥራ የጥበቃ አገልግሎት  ለሚሠጥ “ትረስት የጥበቃና የሰው ኃይል አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” ከተሰኘው ድርጅት ጋር ውል በማድረግ ሥራውን ያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ የሥራ ውሉ የተቋረጠው በሕግ አግባብ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡ ግራ ቀኙን ያከራከረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 11314 በ13/9/2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት ስንብቱ ከሕግ ውጪ ነው የ6 ወር ደመወዝ ካሳ እና የእረፍት ጊዜ ክፍያ ተከፍሎአቸው ይሰናበቱ ስል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤትም በዚህ በፍ/ቁጥር 67186 ሰኔ 9 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ6 ወር ደመወዝ ካሳ ተከፍሎአቸው ይሰናበቱ ተብሎ የተሠጠውን ውሳኔ ለማጣራት ያስቀርባል እንደገና ተመልሶ እና ትዕዛዙ የ6 ወር ካሳ ክፍያን አይመለከትም ሌሎች ውሳኔዎችን አጽንቼአለሁ ስል ትዕዛዝ በመስጠቱ የቀረበ የሰበር አቤቱታ ነው፡፡

      አመልካች ሰኔ 10 ቀን 2000 ዓ.ም ጽፎ ያቀረበው ዋና ቅሬታ ስንብቱ የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ የአሠራር ዘዴ ለመለወጥ የተደረገ በመሆኑ ከሕግ ውጪ ነው መባሉና የ6 ወር ደመወዝ ካሳ እንዲከፈል የተሠጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ እንዲሻርልን የሚል ነው፡፡

      በዚህ ፍ/ቤትም የተጠሪዎች ስንብት ያለአግባብ ነው ተብሎ የተሠጠው ውሳኔ በአግባቡ መሆኑ አለመሆኑን ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ታዞ ተጠሪዎች ሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም የተፃፈ መልስ በማቅረብ ውሳኔው እንዲፀና ተከራክረዋል፡፡እኛም የግራ ቀኙን ክርክር በሕግ ረገድ እንደሚከተለው መርምረናል፡፡

      የሥራ ውል ሊቋረጥ የቻለው ተጠሪዎች ይሠሩብት የነበረው የጥበቃ ሥራ ለሌላ የጥበቃ አገልግሎት ለሚሠጠው ድርጅት በመተላለፍ ምክንያት እንደሆነ በተጠሪዎችም አልተካደም ፡፡ ይህ ከታመነ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 መሠረት አሠሪው አዲስ አሰራርን ለመከተል የድርጅቱን ምርታማነት ለማሻሻልና የአሠራር ዘዴዎች በመለወጡ ምክንያት ሠራተኞቹ ይሠሩበት የነበረው የሥራ መደብ ቢሠረዝ አሠሪው ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውል ለማቋረጥ እንደሚችል በግልጽ ተደንግጓል፡፡ የበታች ፍ/ቤት ስንብቱ ከሕግ ውጪ ነው ለማለት መሠረት ያደረገው አመልካች የጥበቃ ሥራ በሌላ 3ኛ ወገን እንዲከናወን ተደርጓል ከሚል በስተቀር የሥራ መደቡ ተሠርዟል የሚል ባለመሆኑ በአዋጅ አንቀጽ 28 ትርጉም ሊሠጠው የሚችል አይደለም የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው በማለት ነው፡፡ በመሠረቱ አመልካች የሥራ መደቡን ለሌላ ድርጅት ሲሠጥ የጥበቃዎቹ ቅጥር፣ዕድገት፣ዝውውር፣ስንብትና ክፍያ የሚፈፀመው በዚያው ድርጅት ነው ፡፡ አመልካች የሥራ መደቡን ሠርዞ ያስተላለፈ በመሆኑ በቃል የክፍያ ስምምነት በማድረግ ለድርጅቱ የሚከፍል ስለሆነ ሥራው የሚያከናውነው በሌላ ድርጅት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ በተያዘው ለውሳኔው መሠረት መሆን የሚገባው የሥራ መደቡ መሠረዝ ወይም አለመሠረዝ ብቻ ሳይሆን ስንብቱ ሕጋዊ ነው ወይንስ ከሕግ ውጪ ነው የሚለው ጭብጥ ሆኖ አመልካች የመልስ ሰጭዎችን/የተጠሪዎችን/ የሥራ ውል ለማቋረጥ ሕጋዊና በቂ ምክንያት መኖሩን ማስረዳት ነው፡፡ አመልካች አከራካሪ የሆነውን የሥራ መደብ ለሌላ አካል ማስተላለፍን ተጠሪዎች በክስ ማመልከቻቸውም ላይ የጠቀሱትና ያልተካደ በመሆኑ ሥራን  ለሌላ ማስተላለፍ /0ut sourcing/  ሕጋዊ ነው፡፡ ይህ ከሕግ ወጪ ነው የሚል ወገን አለመተላለፍን ማስረዳት ብቻ ነው፡፡ ይህ ክርክር የለም ምናልባት አመልካች ለተጠሪዎች ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ማሰናበቱ የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው  ወደ ሚለው መደምደሚያ የሚያደርስ ሳይሆን ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ማቋረጥ ውጤቱ ለሠራተኛው ሊከፈለው  የሚገባውን የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ እንዲከፈላቸው ሕጉ ከሚያስገድድ በስተቀር የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው ወደ ሚለው የተለጠጠ የሕግ ትርጉም ላይ የሚያደርስ አይሆንም፡፡

      ለማጠቃለል የሥራ መደብ በሌላ 3ኛ ወገን እንዲከናውን አሳልፎ መስጠት/0ut sourcing/ በውጫዊ እይታ ሲታይ የሠራተኛውን መብት የሚነካ ቢመስልም በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ረገድ ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም የተጠሪዎች የሥራ ውል የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ነው በማለት የ6 ወር ደመወዝ ካሳ ተከፍሎአቸው ይሠናበቱ በማለት የተሠጠው ውሳኔ ከላይ በተመለከቱ ምክንያቶች መሠረታዊ የሕግ ትርጉም ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት የሚከተለውን ውሳኔ ሠጥተናል፡፡

                              ው ሳ ኔ

1. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 11314 በ 13/9/2000 ዓ.ም  ስንብቱ ከሕግ ውጪ ነው በማለት የ6 ወር ደመወዝ ካሳ ተከፍሎአቸው ይሠናበቱ ሲል የሠጠው ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡ይፃፍ፡፡

2.  ስንብቱ በሕግ አግባብ ነው ብለናል፡፡

3.  በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 35 መሠረት የማስጠንቀቂያ ሊከፈላቸው ይገባ የነበረውን እንደየአገልግሎት ዘመናቸው አንፃር ሊከፈላቸው ይገባል ብለናል፡፡

4.  ተጠሪዎች ከ9/12/98/ እስከ ጥር 25 ቀን 1999 ዓ.ም ድረስ ያለው የእረፍት ቅጣት ክፍያ እንዲከፈል በተሠጠው ውሳኔ ላይ የቀረበ አቤቱታ ስለሌለ ፀንቷል፡፡

5.  ወጪና ኪሳራ የዚህ ፍ/ቤትን ግራ ቀኙ ይቻቻሉ ብለን መዝገቡን ዘግተናል፡፡

 

                                የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

መ/ት

No comments:

Post a Comment