Tuesday, September 15, 2020

የአክሲዮን ማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄ- በቂ ምክንያት- ሰ/መ/ቁ. 127352 ቅፅ 22

 

የሰበር መዝገብ ቁጥር 127352

መስከረም 22 ቀን 2010  ዓ.ም.

ዳኞች፡-ፀጋይ አስማማው አልማው ወሌ

ሙስጠፋ አህመድ

አብርሃ መሰለ

ሰናይት አድነው

አመልካቾች፡-

1.       አቶ ታደሰ አይችሉህም

2.       አቶ ደሳለኝ አስራደ       የቀረበ የለም

3.       አቶ ንጉሴ አማረ

4.       አቶ መስፍን በጋሻው  ተጠሪ፡-አቶ ዘውዴ ታደሰ የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የአክሲዮን ማህበር ይፍረስልኝ ጥያቄን አስመልክቶ የተነሳ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን አመልካቾቹ የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡት  በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 18932 በ09/06/2008 ዓ.ም. ተሰጥቶ  በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 67288 በ13/08/2008 ዓ.ም. በፍርድ የጸናው  ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ነው።

ተጠሪው በ19/04/2008 ዓ.ም. በተጸፈ ማመልከቻ እንደቀደም ተከተላቸው 1ኛ፣2ኛ፣5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በነበሩት የአሁኖቹ አመልካቾች እና የዚህ ሰበር ክርክር ተካፋይ ባልተደረጉት አቶ አባስ መሐመድ እና አቶ ገደፋው ጌጡ በተባሉ የስር 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ላይ ክስ ያቀረቡት ከሳሽ እና ተከሳሾች በጋራ በመሆን የትምህርት ተቋማትን የማቋቋም ዓላማ ያለው አክታ ጠቅላላ ንግድ አክሲዮን ማህበር በመስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ማቋቋማቸውን፣በዚሁ መሰረትም ማህበሩ አክታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ መሆኑን፣ማህበሩን በስራ አኪያጅነት የሚመሩትም ከሳሽ መሆናቸውን፣በማህበሩ እንቅስቃሴ ላይ ለመወያየት ከሳሽ በተደጋጋሚ ስብሰባ ቢጠሩም ተከሳሾቹ ለመገኘት ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን እና በትምህርት ቤቱ የስራ እንቅስቃሴ ምክንያት ከሳሽ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በነበረበት ጊዜ እንኳ ተከሳሾቹ ስለጉዳዩ ቀርበው ያልጠየቁ መሆኑን እና እነዚህ ሁኔታዎችም  በንግድ ሕጉ መሰረት ማህበሩን ለማፍረስ በቂ ምክንያት መሆናቸውን በመግለጽ ማህበሩ እንዲፈርስ እና አስተዳዳሪ ተሾሞለት ሂሳቡ እንዲጣራ እንዲደረግ እንዲወሰንላቸው በመጠየቅ ነው።

የስር 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በ10/05/2008 ዓ.ም.በሰጡት መልስ የከሳሹ ጥያቄ የእነርሱም ጥያቄ በመሆኑ በክሱ መሰረት ቢወሰን ተቃውሞ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን የአሁኖቹ አመልካቾች በበኩላቸው በ17/05/2008 ዓ.ም. በሰጡት መልስ ክሱ ሊቀርብ የሚገባው በማህበሩ ላይ እንጂ በእኛ በአባላቱ ላይ አይደለም፣ከሳሽ በተከሳሾቹ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብትና ጥቅም የላቸውም የሚሉ የመቃወሚያ ነጥቦችን ካስቀደሙ በኃላ ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ስብሰባ የመጥራት ስልጣን የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እንጂ የከሳሹ አለመሆኑን፣ከሳሹ ስብሰባ ለመጥራት የሚያስችል ስልጣን ነበራቸው ቢባል እንኳ በሕጉ አግባብ ያከናወኑት ጥሪ አለመኖሩን፣የስብሰባ አለመደረግም ሆነ በቁጥጥር ስር ሲውል አልጠየቃችሁኝም በማለት ከሳሹ በክሱ የጠቀሷቸው ምክንያቶች በንግድ ሕጉ መሰረት አንድን ማህበር ለማፍረስ የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አለመሆናቸውን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ተከራክረዋል።  

ፍርድ ቤቱም የመጀመሪያ ደረጃ የመቃወሚያ ነጥቦችን በብይን አልፎ በፍሬ ጉዳዩ ረገድ ክሱን ከሰማ በኃላ የግራ ቀኙን አጠቃላይ ክርክር እና ማስረጃ መርምሮ አክሲዮን ማህበሩ ከተመሰረተበት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባም ሆነ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄዶ እንደማያውቅ በተከሳሾቹ ያልተካደ መሆኑን፣እነዚህ ምክንያቶች ደግሞ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ14፣በንግድ ሕግ ቁጥር 217 (2)፣218 (2) እና 495 (3) መሰረት ማህበሩ እንዲፈርስ ለመወሰን የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች መሆናቸውን፣3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችም  በክሱ መሰረት ቢወሰን ተቃውሞ እንደሌላቸው የገለጹ መሆኑን በዝርዝር አስፍሮ አክሲዮን ማህበሩ ትምህርት ቤት ከሚዘጋበት ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲፈርስ፣አስተዳዳሪ እንዲሾም እና ንብረቱ እንዲጣራ ውሳኔ ሰጥቶአል።በአሁኖቹ አመልካቾች  ጠያቂነት ይግባኙን የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ በፍርድ ያጸናው ይህንኑ ውሳኔ ሲሆን አመልካቾቹ ለዚህ ችሎት ያቀረቡት  የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ አክሲዮን ማህበሩ ባልተከሰሰበት የማህበሩ አባላት ተከሰው ማህበሩ እንዲፈርስ የመወሰኑን አግባብነት ከንግድ ሕግ ቁጥር 495 ድንጋጌ አንጻር ተጠሪው ባሉበት ለመመርመር እንዲቻል ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።

የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ነጥብ አንጻር መርምረናል፡፡

በዚህም መሰረት ተጠሪው በ19/04/2008 ዓ.ም.ባቀረቡት ክስ ማህበሩን ለማፍረስ የሚያስችል ነው በማለት የጠቀሷቸው ምክንያቶች ተጠሪው በማህበሩ ስራ አስኪያጅነታቸው ባደረጉት ጥሪ መሰረት የማህበሩ አባላት በስብሰባ ለመገኘት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል፣ ከማህበሩ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ተጠሪው በስራ አስኪያጅነታቸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በነበረበት ጊዜ የማህበሩ አባላት ቀርበው ስለጉዳዩ አልጠየቁም፣ዋስትና ለመግባትም ፈቃደኛነታቸውን አልገለጹም የሚሉ መሆናቸውን፣ማህበሩ ከተመሰረተበት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባም ሆነ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ተከናውኖ አያውቅም  የሚሉት ምክንያቶች በተጠሪው በኩል የቀረቡት በክስ ማመልከቻው ላይ ተገልጸው ሳይሆን ክሱ በተሰማበት ጊዜ በተደረገ ክርክር መሆኑን፣የስር ፍርድ ቤቶችም ማህበሩ እንዲፈርስ ለመወሰን የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች ናቸው በማለት የተቀበሉት ክሱ በተሰማበት ጊዜ በተጠሪው በኩል የቀረቡትን ምክንያቶች መሆኑን፣ማህበሩ ከተመሰተረበት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድም ሆነ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አለመኖሩ በአመልካቾቹ ያልተካደ መሆኑን እና ይሁን እንጂ ክሱ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ማህበሩ ያቋቋመው ትምህርት ቤት የስራ እንቅስቃሴ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በሆኑት ተጠሪ አማካይነት ሲከናወን የቆየ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።

የንግድ ሕጉ በአንድ በኩል ለሁሉም ዓይነት የንግድ ማህበራት ተፈፃሚነት ያላቸውን የማፍረሻ ምክንያት ያካተተ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱ ዓይነት ንግድ ማህበር ካለው የተለየ ባህሪ አንጻር ለየማህበሩ ተፈጻሚ የሚሆኑ ተጨማሪ የማፍረሻ ምክንያቶችን አካቶ ይዞአል፡፡በንግድ ሕጉ ስለ ንግዱ ማህበራት በጠቅላላው በሚናገረው ክፍል ከሚገኙት ቁጥር 217 እና 218 ድንጋጌዎች በተጨማሪ የአክሲዮን ማህበራት የሚፈርሱባቸው ምክንያቶች በንግድ ሕጉ በቁጥር 495 (1) ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ።እነርሱም፡-

(ሀ) በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማኅበሩ እንዲቀጥል ካልተወሰነ በቀር በመመስረቻ ጽሁፍ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣

(ለ)  ማህበሩ የተቋቋበት ስራ ሲያልቅ፣

(ሐ)  በነገሩ መጥፋት ወይም የማህበሩ ጉዳይ (ዓላማ) ሊደረስበት የማይቻል ሲሆን፣

(መ)  አስቀድሞ እንዲፈርሱ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ፈቅዶ ሲወስን፣

(ሠ) ከማህበረተኞቹ አንዱ ባቀረበው በቂ ምክንያት ማህበሩ እንዲፈርስ ፍርድ ቤቱ ሲያዝ

(ረ) በቁጥር 311 የተደነገጉት ውሳኔዎች እንደተጠበቁ ሆነው አክሲዮኖቹ ሁሉ በአንድ ማህበረተኛ እጅ ሲጠቃለሉ፣

(ሰ)  የኪሳራ ክስ ሲጀመር እና

(ሸ)  ከማህበሩ ዋና ገንዘብ ሶስቱ ሩብ ሲጠፋየሚሉ ናቸው።

ተጠሪው ካቀረቡት ክስ አንጻር ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ለጉዳዩ አግባብነት ያለው “ከማህበረተኞቹ አንዱ ባቀረበው በቂ ምክንያት ማህበሩ እንዲፈርስ ፍርድ ቤቱ ሲያዝ” በሚል የተገለጸው ምክንያት ነው።ለክርክሩ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ አክሲዮን ማህበሩ ባልተከሰሰበት የማህበሩ አባላት ተከሰው ማህበሩ እንዲፈርስ የመወሰኑን አግባብነት ከንግድ ሕግ ቁጥር 495 ድንጋጌ አንጻር ለማጣራት የሚል ነው።አንድ ማህበር እንዲፈርስ ክስ በሚቀርብበት ጊዜ እንደየክርክሩ ባህርይ እና እንደየአስፈላጊነቱ ማህበሩ የክርክሩ ተካፋይ መደረግ እንደሚገባው የሚታመን ቢሆንም ቁጥር 495 ድንጋጌ የማህበሩን የክርክር ተካፋይ መደረግ ጉዳይ አስመልክቶ የሚገልጸው ነገር የለም።በመሆኑም በጉዳዩ እልባት ማግኘት የሚገባው ማህበሩ ከተመሰረተበት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድም ሆነ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አለመኖሩ የአክሲዮን ማህበሩ እንዲፈርስ ለመወሰን የሚያሰችል በቂ ምክንያት ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ዓቢይ ነጥብ ነው።ከድንጋጌው አነጋገር እንደሚታየው ከማህበርተኞቹ አንዱ ባቀረበው በቂ ምክንያት ማህበሩ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሊፈርስ እንደሚችል ከመገለጹ በቀር በቂ ምክንያት ተብለው የሚወሰዱትን ሁኔታዎች ድንጋጌው ለይቶ አያመለክትም።በመሆኑም ማህበሩ እንዲፈርስ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት ነው በሚል ከማህበረተኞቹ በአንዱ የሚቀርበው ምክንያት በርግጥም በቂ መሆን አለመሆኑ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ሊጤን ይገባል።

በመሰረቱ የንግድ ማህበራት ለአባላቱ ትርፍ ከማስገኘት ዓላማ ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገንቢ ሚና የሚጫወቱ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።የሕግ ጥበቃም አላቸው።በተያዘው ጉዳይ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው የአክሲዮን ማህበር በትምህርት ዘርፍ የተሰማራ መሆኑ እና ትምህርት ቤት በማቋቋም ወደ እንቅስቃሴ የገባ መሆኑም ተረጋግጦአል።ይህም የማህበሩ ሕልውና ጉዳይ በተቀጣሪ ሰራተኞች፣በተማሪዎች እና በአካባቢው የትምህርት እንቅስቃሴ ላይ ጭምር በአንድ ወይም በሌላ አግባብ ተጽዕኖ የሚኖረው መሆኑን የሚያመለክት ነው።በመሆኑም የማህበሩ መፍረስ አለመፍረስ ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ በቀረበ ጊዜ እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ከግምት መግባት የሚገባቸው መሆኑን እና ማህበሩ እንዲፈርስ ሊወሰን የሚገባው ተከሰተ የተባለውን ችግር ማህበሩ እንዲፈርስ በመወሰን ካልሆነ በስተቀር በሌላ የሕግ አግባብ መፍታት ወይም ማስወገድ እንደማይቻል ሲረጋገጥ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ማህበሩ ከተመሰተረበት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባም ሆነ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አለመኖሩ የተረጋገጠ ቢሆንም ማህበሩ ያቋቋመው ትምህርት ቤት እንቅስቃሴ ግን ስራ አስኪያጁ መደበኛ ባልሆነ መንገድም ቢሆን ከማህበሩ አባላት ጋር በሚያደርጉት ውይይት እየተከናወነ የነበረ መሆኑ ተረጋግጦአል። ተጠሪውም በክስ ማመልከቻቸው ስብሰባ ጠርቼ አባላቱ አልተገኙም ከማለት በቀር የዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀው የነበረ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም። የስር ፍርድ ቤቶችም በዚህ ረገድ ያረጋገጡት ፍሬ ነገር ስለመኖሩ የመዝገቡ ግልባጭ አያመለክትም። የዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀው ነገር ግን ስብሰባ የመጥራት ስልጣን ያለው የማህበሩ አካል ስብሰባውን ለመጥራት ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረ መሆኑ ቢረጋገጥ እንኳ ይህ መሆኑ የዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲከናወን ጥያቄ አቅርቦ ለማስወሰን የሚያስችል ከሚሆን በቀር በቀጥታ ማህበሩ እንዲፈርስ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው አይደለም። የሀዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርዱ ለይ በጠቀሰው የንግድ ሕግ ቁጥር 495 (3) ስር የተጠቀሱት ፍሬ ነገሮች የተረጋገጡ ስለመሆኑም መዝገቡ አያመለክትም። በመሆኑም ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ አለመደረግ ጉዳይ በሌላ የሕግ አግባብ ሊፈታ የሚችል ችግር ሆኖ እያለ በስር ፍርድ ቤቶች በቀጥታ አክሲዮን ማህበሩን ለማፍረስ እንደሚያስችል በቂ ምክንያት ተወሰዶ ማህበሩ እንዲፈርስ የተሰጠው ውሳኔ አግባብነት ያላቸውን የንግድ ሕጉን ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገ እና ማህበሩ የተቋቋበትን ዓላማ እንዲሁም የማህበሩ መፍረስ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ውጤቶች ያላገናዘበ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው ነው ለማለት የሚያስችል ሆኖ አልተገኘም።

ሲጠቃለል አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።

ው ሳ ኔ

1.       በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 18932 በ09/06/2008 ዓ.ም. ተሰጥቶ  በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 67288 በ13/08/2008 ዓ.ም. በፍርድ የጸናው  ውሳኔ  በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሮአል።

2.       ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ወይም የማህበሩ የጠቅላላ ጉባኤ  አለመደረግ በሌላ የሕግ አግባብ ሊፈታ የሚችል ችግር እንጂ በቀጥታ ማህበሩ እንዲፈርስ ለመወሰን የሚያስችል በቂ ምክንያት አይደለም በማለት ወስነናል።

3.       ተጠሪውም ሆኑ የማህበሩ ሌላ አባል የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ወይም የማህበሩ የጠቅላላ ጉባኤ በፍርድ ኃይል እንዲከናወን ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም።

4.       እንዲያውቁት የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍርድ ቤቶች ይላክ።

5.       በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 18932 የተያዘው ክርክር ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ በ01/10/2008 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቶአል።

6.       የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪ እና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ። 

7. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል። 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አበለት 

መ/ይ 

No comments:

Post a Comment