Tuesday, September 15, 2020

የውርስ ማጣራት ውስጥ ተካፋይ የሆነ ሰው ስለሚያቀርበው የጣልቃገብነት አቤቱታ- ሰ/መ/ቁ.133708 ቅፅ 22

የሰ/መ/ቁ.133708 ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም

 

ዳኞች፡- ፀጋይ አስማማው       ሙስጠፋ አህመድ      አብርሃ መሰለ        ጳውሎስ ኦርሺሶ        ሰናይት አድነው     

አመልካቾች፡- 1. ወ/ሮ ጣይቱ ደያሳ

2.         ወ/ሮ ዘነቡ ደያሳ

3.         አቶ አሸናፊ ደያሳ

4.         ወ/ሮ ዘር ደያሳ

5.         ወ/ሮ ሽዋዬ ለገሰ

6.         ወ/ሮ ዲባቤ ለገሰ     ጠበቃ ጸጋዬ ፈይሳ -ቀረቡ

7.         ወ/ሮ እመቤት ለገሰ

8.         አቶ ካሳ ለገሰ

9.         አቶ መስፍን ረጋሳ

10.     አቶ ደገፋ ረጋሳ

11.     አቶ ሽፈራው ለገሰ

ተጠሪ፡-  አቶ ጉደታ ዲያሳ -ጠበቃ በሬሳ በየነ- ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

     

ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በኦሮሚያ ብ/ክ/መ/ ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን በረክ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት የአሁን አመልካቾች ባቀረቡት አቤቱታ የሟች እናታችን የወ/ሮ ሎሚታ ጉደታ በቀን 22/11/2006 ዓም በውርስ አጣሪዎች የተጣራ የውርስ ንብረት ከተራ ቁጥር 1 እሰከ 17 በመዘርዘር በፍ/ብ/ህ/ቁ.996 መሰረት ተረጋግጦ ማስረጃ እንዲሰጣቸው የጠየቁትን ዳኝነት በመቃወም ተጠሪው የጣልቃ ገብነት ማመልከቻ በቀን 24/02/2007 ዓ.ም አቅርበዋል፤ በዚህ ማመልከቻቸውም አመልካቾች በአቤቱታቸው ከተራ ቁጥር 7 እስከ 10 እንዲረጋገጥላቸው የጠየቁት የባህር ዛፍ፤ የሳር እና የእርሻ መሬት የውርስ ሳይሆን የግሌ በመሆኑ ጣልቃ ገብቼ እንድከራከር እንዲፈቀድልኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ የአሁን ተጠሪ የስር ጣልቃ ገብ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.43 መሰረት ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ሲል ብይን ሰጥተዋል፡፡

የአሁን አመልካቾች የስር ፍርድ ቤት ብይን በመቃወም ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ብይን በመሻር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የአሁን ተጠሪ ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር የወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ የአሁን አመልካቾች ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኋላ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም ሲል በውሳኔ አጽንቶታል፡፡ 

የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካቾች ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል፡፡ አመልካቾችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡  የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡ 

እንደመረመርነውም የአመልካቾች ጥያቄ ተጠሪ የሟች የውርስ ንብረት ከሌሎች ወራሾች ጋር እንዲጣራ በግልፅ ተስማምቶ ውክልና ሰጥቶ በሚጣራው የውርስ ፋይል ተሳታፊ ሆኖ እያለ ቀድሞ የሰጠው ስምምነት ፀፅቶት ውርሱ ሊጣራ አይገባም በይርጋ ይታገዳል በማለት በጣልቃ ገብነት መቀወሚያ በማንሳትና መከራከሩን ከክርክሩ እየታየ ለጉዳዩ አግባብነት የሌላቸው የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41፣43 ድንጋጌዎች በመጥቀስ ተጠሪ ጣልቃ ይግባ መባሉ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ስለሆነ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሊሻር ይገባል የሚል ሲሆን በተጠሪ በኩል ደግሞ በወካይና ተወካይ መካከል ያለው ግንኙነት በቅን ልቦና የተመሰረተ መሆን እንዳለበት እና ተወካዩም የወካዩን ጉዳይ ልክ እንደራሱ ጉዳይ የወካዩን ጥቅም በማስቀደም መስራት እንዳለበት የውክልና ህግ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ አመልካቾች ይህንን የውክልና ስልጣን መከታ በማድረግ የተሰጣቸውን የውክልና ስልጣን በመተላለፍ የእናታችን የውርስ ሀብት ብቻ ሳይሆን በተጠሪ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው የተጠሪን የግል ንብረት እና ይዞታ ጭምረው ለፍርድ ቤት ማቅረባቸው ስህተት ነው፤ የሰጠሁት የውክልና ስልጣን በሌላ ጉዳይ ላይ ሁኖ እያለ ከፍላጎቴና ፍቃዴ ውጭ እንዲሁም በግል ንብረቴ ላይ የቀረበውን ክርክር በተመለከተ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41 ውጭ ጣልቃ ገብቼ ተከራክሬ መብቴን የማስከብርበት ሌላ አመራጭ የለም፤ ስለዚህ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚሁ ረገድ የሰጠው ውሳኔ ስህተት የሌለበት በመሆኑ ሊፀና ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁን ተጠሪ የሟች የውርስ ንብረት ተጣርቶ ክፍፍል እንዲደረግ ከአሁን አመልካቾች ውስጥ ለወ/ሮ ዘርፌ ደያሳ እና ለአቶ ደገፋ ረጋሳ የውርስ መብታቸውን ከሌሎች ወራሾች ጋር እንዲታወቅላቸው የውክልና ስልጣን በመስጠት መሰማማታቸው፤በዚሁ መሰረት ውርስ ንብረት አጣርተው ለፍርድ ቤት ማቅረባቸው፤ የውርስ ማጣራት በሂደት እያለ የአሁን ተጠሪ በስር 3ኛ አመልካች የነበሩት የውርሱ ማጣራት በይርጋ መታገድ አለበት፤ንብረቴ በውርሱ ውስጥ ተጨምሯል የሚሉ ምክንቶች በመዘርዘር በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41 መሰረት ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር መጠየቃቸው ከውሳኔው ግልባጭ ተገንዝበናል፡፡ የሟች የውርስ ንብረት ለማጣራት አመልካቾችና ተጠሪ ጭምር ተስማምተው አጣርተው ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ፍሬ ጉዳዩን የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን በተሰጣቸው የስር ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ተጠሪ አልተስማማሁም በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡  የፍትሀብሔር ህጉ የሟች ውርስ የማጣራት ስልጣን ያላቸውን ግለሰቦች በቅደም ተከተል የሚዘረዝር ሲሆን እነርሱም፡-ሟች በኑዛዜ የውርስ አጣሪ ሆኖ ውርሱን እንዲያጣራ የሾመው ሰው ካለ በመጀመሪያ የውርስ አጣሪ እንደሆነ የፍትሀብሔር ህጉ 948/1/ የሚደነግግ ሲሆን፣ ሟች በውርስ አጣሪነት በኑዛዜ የሾመው ሰው ከሌለ ጠቅላላ የኑዛዜ ተቀባይ የሆነው ሰው የሟችን ውርስ የማጣራት ስልጣን እንዳለው የፍትሀብሔር ሕግ ቁጥር አንቀጽ 948 ንኡስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል፡፡ ሟች በኑዛዜ የመረጠው የውርስ አጣሪ ወይም ጠቅላላ የኑዛዜ ተቀባይ የሌለ በሆነ ጊዜ ሁሉ የሟች ያለኑዛዜ ወራሾች ያላንዳች ፎርማሊቲ የውርስ አጣሪነት ስልጣን እንዳላቸው በፍትሀብሔር ህግ ቁጥር 947 ተደንግጓል፡፡

 

በዚሁ መሰረት አመልካቾች እና ተጠሪ የሟች ያለ ኑዛዜ ወራሾች በመሆናቸው የውርስ አጣሪነት ስልጣን እንዳለቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ነጥብ በውርስ አጣሪ ተጣርቶ ለፍርድ ቤት በቀረበው ሪፖርት ላይ ያላቸውን አስተያየት በመቀበል በውርሱ ማጣራት ሂደት በአግባቡ አልተጣራም የሚል መቃወሚያ ካለም ፍርድ ቤቱ በህጉ መሰረት አጣርቶ ሪፖረቱን ሊያሻሽለው ወይም ሊያፀናው ይችላል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የውርስ አጣሪው ሪፖርት ላይ በተመለከተ ሪፖርቱን በመደገፍ ወይም በመቃወም የሚቀርበው አስተያየት ተቀብሎና መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ከመስጠት ባለፈ የግድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41 መሰረት ተጠሪ በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ለመከራካር ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት የለውም፤ፍርድ ቤቱም ሊቀበለው አይገባም፡፡ ምክንያቱም በአንድ ክስ ሌሎች ተከራካሪ ወገኖች በክርክር ላይ ባሉበት ጊዜ በጉዳዩ ያገባኛል የሚል ማንኛውም 3ኛ ወገን ከፍርድ ውሣኔ በፊት ጣልቃ ገብቶ መከራከር እንደሚችል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 41/1/ ላይ የተደነገገ በመሆኑ ነው፡፡ ተጠሪ በዚሁ ጉዳይ 3ኛ ወገን አይደለም፡፡ ስለዚህ ለተያዘው ጉዳይ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41፤43 አግባበነት ያላቸው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ተጠሪ ከይርጋ ውጭ በሌሎች ነጥቦች ረገድ የውርስ ማጣራቱን ሂደት እና ውጤቱን በተመለከተ አስተያየት መስጠት እና ፍ/ቤቱም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ሊወስን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ተጠሪ የሟች የውርስ ንብረት ተጣርቶ ክፍፍል እንዲደረግ ከአመልካቾች ጋር የተስማማ በመሆኑ የውርስ ማጣራት በይርጋ ይታገዳል በማለት የሚያቀርበው መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም፡፡  ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤቶች በገዳዩ የሰጡት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ስጥተናል፡፡ 


   


1.       የኦሮሚያ ብ/ክ/መ/ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 240200 መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 24107 ህዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በመሻር የኦሮሚያ ብ/ክ/መ/ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 227678 ታህሳስ 14 ቀን 2008 ዓ.ም እና የበረክ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.12792 ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም የሰጡት ውሳኔ በማጽናት የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽለዋል፡፡

2.       ተጠሪ በክርክሩ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.41/43 መሰረት ጣልቃ ይግባ በማለት የሰጡት ውሳኔ ክፍል በመሻር ፤በውጤት ደረጃ ተጠሪ የሟች ውርስ ንብረት ማጣራት በይርጋ ይታገዳል የሚለውን መቃወሚያ ውጭ ያለውን አስተያየት

እንዲያቀርብ መፍቀዳቸው በአግባቡ በመሆኑ አጽንተነዋል፡፡

3.       በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል፡፡የ

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ቅ/ሀ

No comments:

Post a Comment