Tuesday, September 15, 2020

በምትክ ወይም በተለዋዋጭ ስለሚጠየቅ ዳኝነት- ሰ/መ/ቁ.138717 ቅፅ 22

 

የሰ/መ/ቁ.138717

የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ/ም

 

ዳኞች፡1.ፀጋዬ አስማማዉ

2.     ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)

3.     ቀነዓ ቂጣታ

4.     ተሾመ ሽፈራዉ     5. ፀሐይ መንክር

አመልካች፡-   ወ/ሮ ብርክቲ ግደይ -  ጠበቃ አበባ ዘበነ ቀርበዋል    

ተጠሪዎች፡- 1.አቶ ሸምሱ ኑሪ             1ኛ ተጠሪ ቀርበዋል

1.      ወ/ሮ ፈዲላ እስማኤል  ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

ይህ የሰበር ጉዳይ የብድር ዉል የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.185781 በ23/05/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችዉን የሰበር አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ፡፡

 

የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች ከሳሽ፣የአሁን ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ሆነው ሲከራከሩ ነበር፡፡ ከሳሽ ባቀረበችዉ ክስ ተከሳሾች በ16/11/1999 ዓ.ም በተደረገዉ የብድር ዉል ብር 300,000 የተበደሩ ሲሆን በ10/2/2000 ዓ.ም ይህን የብድር ገንዘብ ካልከፈሉ በመያዣነት ያስያዙትን ቤት ስም ሀብት ወደ ከሳሽ ለማስተላለፍ ግዴታ ገብቷል፤ ከሳሽ የቤቱን እዳ ለመንግስት ብር 37,080.40 በተከሳሽ ስም የተከፈለ በመሆኑ፣ የዉስጥ ሁለት በሮችን ለማሰራት ብር 10,000 ያወጣሁ ስለሆነ፣ የቤቱ የመከላከያ ብረት ለማሰራት ብር 2,500 እና ለባለሙያ ብር 1,500 ከፍያለሁ፡፡ ስለዚህ ተከሳሾች ይህን ቤት ስመ ሀብት ወደ ከሳሽ እንዲያዛዉሩልኝ ይህ ካልሆነ ገንዘቡን ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሉኝ፣ በዉሉ መሰረት ግዴታቸዉን ባለመፈጸማቸዉ ገደብ ብር 20,000 እንዲከፍሉኝ በማለት ከሷል፡፡  በዚህ ክስ ላይ የሥር ተከሳሾች ባቀረቡት መልስ የብድር ዉሉን በተመለከተ ተገቢ ነዉ ያሉትን ክርክር በማቅረብ፣ ከሳሽ ለባንክ ከፍያለዉ በማለት እንዲተካላቸዉ /እንዲከፈላቸዉ/ ያቀረቡትን ጥያቄ በሚመለከት ለባንክ የተከፈለዉን ቀሪ እዳ ብር 37,080.40 ለሁለት በሮች ለመከላከያ ብረት የወጣዉ ወጪ በጊዜዉ የነበረዉን ተመጣጣኝ ዋጋ ብንከፍል ተቃዉሞ የሌለን በመሆኑ በዚህ መሰረት ቢወሰን እንስማማለን በማለት ተከራክሯል፡፡

 

ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በመመርመር በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሾች የተበደሩትን ብር 300,000 ለከሳሽ እንዲከፍሉ፤ ከሳሽ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ሚኪሊላንድ ሳይት የሕንጻ የቤት ቁጥር 22 የቤት ቁጥር 843 ለተከሳሾች ሊያስረክቡ ይገባል፣ ለቤቱ አወጣሁ ያሉትን ወጪ በዳኝነት ዉስጥ ስላልጠየቁ ታልፏል በማለት ወስኗል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረበዉን ይግባኝ ዉድቅ በማድረግ የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ ይህን ትዕዛዝ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ፡፡  የአሁን አመልካች መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ አመልካች በመያዣነት የተያዘዉን ቤት በተመለከተ የመንግስት እዳ ብር 37,080.40 እና ቤቱም ወጪ ለበር ብር 10,000 ለመከላከያ ብረት ብር 2,500 ለባለሙያ ብር 1,500 ያወጣነዉን ወጪ እንዲከፈለኝ ጠይቄ እያለሁ፣ ተጠሪዎችም ባቀረቡት መልስ ይህን እዳ እና ወጪዎችን ሳይክዱና ታምኖ እያለ፣ ፍ/ቤቱ ይህን የታመነዉን ጉዳይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.242 መሰረት ወዲያዉኑ ዉሳኔ መስጠት ሲገባዉ ወይም ከዋናዉ ፍርድ ጋር ሊወስንልኝ ሲገባዉ ዳኝነት አልተጠየቀበትም በማለት በማለፍ የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ ይህ ገንዘብ ከወለድ ጋር ታስቦ እንዲከፈለኝ እንዲወሰንልኝ በማለት አመልክቷል፡፡ 

 

የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣የአሁን አመልካች ለባንክ የከፈሉትን እዳ እና ለቤቱ ያወጡትን ወጪዎች ተጠሪዎች የቤቱን ሰነዶች ሲያስረክቡ እንደሚከፍሉ እንደማይቃወሙ፣ ወጪዎችን በተመለከተ ግምቱ የተጋነነ ስለሆነ በነበረዉ የገበያ ዋጋ ተገምቶ ብንከፍል አንቃወምም ብለዉ እያለ በክስ የዳኝነት ክፍል ስላልተጠቀሰ ብቻ ዳኝነት ሳይሰጥበት ዉድቅ የመደረጉን አግባብነት፣ ለመመርመር ሲባል አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡ ባዘዘዉ መሰረት መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርቧል፡፡ የመልሱም ይዘት በአጭሩ፡ በዚህ ጉዳይ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ የቀረበዉ አቤቱታ ዉድቅ እንዲሆንልን በማለት በዝርዝር ተከራክሯል፡፡ የአሁን አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡ 

 

የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነዉ የአሁን አመልካች ባቀረቡት ክስ በብድር ዉል መነሻነት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የተከፈለ እዳ ብር 37,080.40 እና ለቤቱ ያጣሁት ወጪ 4,000 /አራት ሺህ/ እንደከፈሉ በክሱ ዝርዝር ዉስጥ የገለጹ ቢሆንም በዳኝነት ክፍል ሳይጠቅሱ መቅረታቸዉን መገንዘብ ተችሏል፡፡ የአሁን ተጠሪዎች ይህን ክስ በተመለከተ ባቀረቡት መልስ ለባንክ ተከፍሏል የተባለዉን ገንዘብ የካዱት ነገር የለም እንዲሁም ቤቱ ላይ ለተሰሩት ስራዎች የወጣዉን ወጪ በተመለከተ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተገምቶ ቢከፍሉ የማይቃወሙ መሆኑን በመግለጽ ተከራክሯል፡፡ ከዚህ መገንዘብ እንደሚቻለዉ የአሁን ተጠሪዎች ለባንክ የተከፈለዉን ገንዘብ እና ቤቱ ላይ የወጣዉን ወጪ በተመለከተ አምነዉ የተከራከሩ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህን የግራ ቀኛቸዉን ክርክር በሕግ አግባብ ማየቱ አስፈላጊ ነዉ፡፡ 

 

በመሰረቱ ከሳሽ በሚያቀርበዉ የክስ ማመልከቻ ላይ በተለይ ወይም በምትክ ወይም በተለዋዋጭ የሚጠይቀዉን ዳኝነት በግልጽ መጥቀስ እንዳለበት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.224 ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም ከሳሽ የሚጠይቀዉ ዳኝነት ጠቅላላ እንደሆነ የክሱን ጭብጥና የማስረጃዉን አካባቢ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ትክክለኛ መስሎ የታየዉን ፍርድ መስጠት እንደሚችል በዚህ ድንጋጌ ሥር ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል አንድ ተከራካሪ ወገን በመከላከያ መልስ ወይም በማናቸዉም በሌላ መንገድ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ወይም በቃል ክርክር ወቅት የእምነት ቃሉን የሰጠ እንደሆነ፣ ሌላኛዉ ተከራካሪ ወገን በዚህ እምነት መሰረት ዉሳኔ እንዲሰጠዉ መጠየቅ እንደሚችል እና ፍ/ቤትም ሌላ በማስረጃ የሚረጋገጥ ነገር ቢኖርም እንኳን በታመነዉና ዉሳኔ እንዲሰጥበት በተጠየቀዉ ጉዳይ ብቻ ፍርድ መስጠት እንደሚገባዉ

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.242 ሥር ተመልክቷል፡፡ 

 

በዚህ አግባብ አሁን ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ የአሁን አመልካች በብድር ዉል ምክንያት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የከፈሉትን ገንዘብ እና ከቤቱ ጋር በተያያዘ ለተሰሩት ሥራዎች ያወጡትን ወጪዎች በክሳቸዉ ዝርዝር ዉስጥ ገልጸዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የሥር ፍ/ቤት አመልካች ቤቱን ለተጠሪዎች የሚመልሱበት ሁኔታ መኖሩን እስከተገነዘበ ድረስ አመልካች ከቤቱ ጋር በተያያዘ አዉጥቻለሁ፣ ከፍያለሁ በማለት በክስ ማመልከቻ ላይ እስከጠየቁ ድረስ የሥር ፍ/ቤት አመልካች ይህ ገንዘብ እንዲከፈላቸዉ በዳኝነት ክፍል ዉስጥ አልጠየቁም የሚል ከሆነ ስለጉዳይ በሕግ አግባብ ግልጽ እንዲያደርጉ ማድረግ የሚከለክለዉ ነገር አልነበረም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሁን ተጠሪዎች ባቀረቡት መልስና የቃል ክርክር አመልካች የጠየቀችዉን ይህን ገንዘብ የካዱት ነገር የለም፡፡ የአሁን ተጠሪዎች ከዚህ ቤት ጋር በተያያዘ ለባንክ የተከፈለዉን እዳ እና ለቤቱ የወጣዉን ወጪ አምነዉ እና ለመክፈልም ፈቃደኛ እንደሆኑ ገልጸዉ እስከተከራከሩ ድረስ፣ የሥር ፍ/ቤቶች ከፍ ሲል በተጠቀሰዉ የህግ ድንጋጌ በእምነት ቃላቸዉ አግባብ ዉሳኔ መስጠት ይገባቸዉ ነበር፡፡ 

 

ሲጠቃለል የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተጠሪዎች እምነት መሰረት ይህን ገንዘብ ለአመልካች እንዲከፍሉ ዉሳኔ መስጠት ሲገባዉ በክሳቸዉ የዳኝነት ክፍል ዉስጥ ይህ ገንዘብ እንዲከፈላቸዉ አልጠየቁም በሚል ምክንያት ዉድቅ በማድረግ ዉሳኔ መስጠቱ እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይህን ማረም ሲገባዉ ሳያርመዉ የሥር ዉሳኔ በማጽናት መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆኑ የሚከተለዉ ተወስኗል፡፡ ዉ ሳ ኔ

1.          የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ.61912 በ3/2/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና ይህን ዉሳኔ በማጽናት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.185781 በ23/5/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሻሽሏል፡፡

2.          የአሁን አመልካች በብድር ዉል ምክንያት የያዙትን ቤት በተመለከተ ለባንክ የከፈሉትን እና ለቤቱ ያወጡትን ወጪ በድምሩ ብር 41,080.40 /አርባ አንድ ሺህ ሰማንያ ከአርባ ሳንቲም/ እስከተረጋገጠ ድረስ፣ የአሁን ተጠሪዎች ይህን ገንዘብ ለአመልካች ሊከፍሉ ይገባል ብለናል፡፡ ነገር ግን የአሁን አመልካች በዚህ ገንዘብ መጠን የዳኝነት ክፍያ ያልከፈሉ እንደሆነ ባለዉ የዳኝነት ክፍያ ታሪፍ ደንብ መሰረት ሊያከፍሉ ይገባል ብለናል፡፡

3.          የሥር ፍ/ቤቶች አመልካች በብድር ዉል ምክንያት የያዙትን ቤት ለተጠሪዎች እንዲያስረክቡ እና ተጠሪዎች ደግሞ በብድር ዉሉ መሰረት የተበደሩትን ገንዘብ ለአመልካች እንዲከፍሏቸዉ በማለት የሰጡት የዉሳኔ ክፍል አልተነካም፣ ጸንቷል፡፡ 

4.          የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ፡፡ 

5.          ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ማ/

No comments:

Post a Comment