Wednesday, September 9, 2020

ከውል ውጭ ሃላፊነት- የመኪና አደጋ- ጥቅም የሌለው ግንኙነት ሰበር መ/ቁ 47627

 የሰበር መ/ቁ 47627

ሚያዝያ 18 ቀን 2002 ዓ/ም

 

ዳኞች፡- 1. ሂሩት መለሰ

       2. ተሻገር ገ/ሥላሴ

       3. ታፈሰ ይርጋ

       4. አብዱራሂም አህመድ

       5. አልማው ወሌ

 

አመልካች፡- የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን - የቀረበ የለም

ተጠሪ፡- 1. ኮ/ል ፈቃዱ ጋሎ - በሌሉበት የሚታይ ነው

       2. በፈቃዱ አንጀሎ - ቀረቡ

 መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍ ር ድ

     ጉዳዩ ከውል ውጪ ኃላፊነትን መሰረት ያደረገ የካሳ ክፍያን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች ባሁኑ አመልካች ላይ በደ/ብ/ብ/ሕ/ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ ነው፡፡ የተጠሪዎች የክስ ይዘትም ባጭሩ ንብረትነቱ የአመልካች በሆነውና በአመልካች ሾፌር ይሽከረከር በነበረው የጭነት መኪና ላይ ተሳፍረው በመጓዝ ላይ እንዳሉ ባልታወቀ ምክንያት መኪናው የመገልበጥ አደጋ ደርሶበት ተጠሪዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደረገ መሆኑንና የደረሰባቸውን የጉዳት መጠንና የካሳ መጠን በመዘርዘር ባጠቃላይ ብር 90,000.00(ዘጠና ሺህ ብር) አመልካች እንዲከፈላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኑ አመልካችም ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስ በወቅቱ መኪናን ያሽከረክር የነበረ ሹፌር አለመከሰሱ ያላግባብ መሆኑን፣ መኪናው የጭነት መኪና ሁኖ ተጠሪዎች ለራሳቸው ስራ በፍላጎታቸው ተሳፍረው ሲጓዙ ለደረሰው አደጋ ምንም ጥቅም ያላገኘው የመኪናው ባለንብረት ተጠያቂ የሚሆንበት ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩን፣ እንዲሁም የጉዳትና ካሳ መጠኑና በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በመጥቀስ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች በመገልበጥ ተጠሪዎች ላይ አደጋውን ያደረሰው መኪና ባለንብረት በመሆኑ በተጠሪዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት እንደአለበት፣ የካሳ መጠኑም በርትዕ ለእያንዳንዳቸው ብር 10,000.00(አስር ሺህ ብር) ሊሆን እንደሚገባ በመግለፅ አመልካች ተጠሪዎችን እንዲክስ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤት አመልካችን ከጉዳቱ ኃላፊነት አለበት በማለት የሰጠውን የውሳኔ ክፍል በመቀበል የካሳ መጠኑን ብቻ አሻሽሎ ለ1ኛ ተጠሪ ብር 4000.00 (አራት ሺህ)፣ ለ2ኛ ተጠሪ ደግሞ ብር 5000.00(አምስት ሺህ ብር) እንዲከፈላቸው ሲል ወስኗል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

     የአመልካች ነገረ ፈጅ ሐምሌ 17 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፉት ሁለት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪዎች ተሳፍረው የነበሩት የአመልካች መኪና የጭነት ሁኖ አመልካች ምንም ጥቅም ሳያገኝበት ለጉዳቱ ኃላፊ ነው ተብሎ መወሰኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089(1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ያላገናዘበ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊ ተብሎ መወሰኑ ይሕ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 38456 ከሠጠው የሕግ ትርጉም አንፃር ሲታይ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጎአል፡፡ በዚህም መሰረት ለተጠሪዎች መጥሪያ ተልኮላቸው 1ኛ ተጠሪ በጥሪው መሰረት ስላልቀረቡ ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ ቀርበው የጽሑፍ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡

     የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተደረገው ሲሆን ይህ ችሎትም ጉዳዩን ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘበ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

     ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪዎች ለክሳቸው መሰረት ያደረጉት ከውል ሃላፊነትን የሚገዛውን የፍትሐብሔር ሕግ ክፍልን መሆኑን፣ ተጠሪዎች ደረሰብን ያሉት ጉዳት የደረሰው በአመልካች መኪና በመገጨታቸው ሳይሆን በመኪናው ላይ ተሳፍረው ሲሄዱ መኪናው በመገልበጡ ምክንያት መሆኑንና መኪናው ንብረትነቱ የአመልካች ሁኖ አገልግሎቱም የጭነት እንጂ ሰውን ለማጓጓዝ አለመሆኑን፣ ተጠሪዎች በመኪናው ላይ በመሳፈራቸውም አመልካች ያገኘው ጥቅም አለመኖሩን ነው፡፡

     በመሰረቱ የመኪናው ባለቤት መኪናው በ3ኛ ወገን ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ጥፋት ባይኖርበትም የመኪናው ባለቤት በመሆኑ ብቻ ኃላፊ የሚሆንበት አግባብ ስለመኖሩ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2081(1) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያሳያል፡፡ ይህ በአጠቃላይ የተቀመጠ መርህ ሲሆን የመኪናው ባለቤት ከኃላፊነት የሚድንበት ልዩ ሁኔታ ስለመኖሩ ደግሞ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2084 እና 2089 ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡ ለተያዘው ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው ልዩ ሁኔታ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089(1) ስር የተመለከተው ሲሆን የድንጋጌው ሙሉ ይዘት ሲታይም ጉዳቱ የደረሰው ጥቅም በሌለው ግንኙነት በሆነ ጊዜ የመኪናው ወይም ጉዳቱን ያደረሰው ንብረት ባለቤት ኃላፊነት አይኖርበትም በሚል የተቀመጠ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ከላይ እንደተገለፀው እና በበታች ፍርድ ቤቶች እንደተረጋገጠው ፍሬ ነገር አመልካች ተጠሪዎች በጭነት መኪናው በመሳፈራቸው ያገኘው ጥቅም የለም ወይም ተጠሪዎች በአመልካች መኪና የተገለገሉት በአመልካች ጥቅም በሚያስገኝ ሁኔታ አይደለም፡፡ አመልካች የፈፀመው ጥፋት ስለመኖሩም የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም የመኪናው ባለንብረት ለጉዳቱ ኃላፊነት የሌለበት መሆኑን ይህ ሰበር ችሎት ተመሳሳይ ጉዳይ በመ/ቁጥር 38457 ቀርቦለት በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኘውን ፍርድ ቤት የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካችን ለጉዳቱ ኃላፊ ያደረጉት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089(1) ድንጋጌን ባላገናዘበ መልኩ ሁኖ ስለአገኘነው ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

1.  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 03181 መጋቢት 12 ቀን 2000 ዓ/ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 66635 ግንቦት 14 ቀን 2ዐዐ1 ዓ/ም ተሻሽሎ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡

2.  በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089(1) መሰረት አመልካች በተጠሪዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆንበትና ካሳ የሚከፈልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ብለናል፡፡

3.  ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

ራ/ታ

No comments:

Post a Comment