Saturday, October 17, 2020

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1115-2011

 

አዋጅ ቁጥር 1115/211

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን

እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ

 

የአገሪቱን ልማት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ እና የሕዝቦችን በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የዜና አገልግሎት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደ አገራዊ የዜና አገልግሎት የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ መወጣት የሚያስችለው ተቋማዊና የአሰራር ነፃነት እንደዚሁም የተሻለ የሕግ ጥበቃ እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ፤

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ ባህሪውን ባገናዘበ መንገድ እንዲመራ እና የስራ እድገትና ቅልጥፍናው በተሻለ መንገድ እንዲራመድ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አሰራርና አደረጃጀት ከአለምአቀፍ የቴክኖሎጂና ሙያዊ እድገት ጋር የተጣጣመና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

 

ለስራና ሠራተኛ አመቺ የሆነ የስራ አካባቢን መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

 

ዋና ዋና አገራዊ ሁነቶችንና ክስተቶችን በፅሁፍ፣ በድምፅ፣ በፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል በማስደገፍ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስራዎች ለምርምርና ጥናት ግብዓትነት እንዲውሉ ሰንዶ የማስቀመጥ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ተቋሙ ራሱን በገቢ መደገፍ እንዲችል ገቢ የሚያመነጭባቸው ስራዎች ላይ መሳተፍ የሚያስችለው ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲን እንደገና በማቋቋም ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት የበለጠ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

 

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።

 

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

 

1. አጭር ርዕስ

 

     ይህ አዋጅ "የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1115/2011" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

 

2. ትርጓሜ

 

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፣

 

1/ ዜና ማለት በበርካታ ሰዎች ወይም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ አውንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥርን አዲስ ክስተት የሚያመለክት፣ ተሞክሮ ማስተላለፍ የሚችል፤ የታዳሚዎችን ፍላጎት በማሟላት ህዝቦችን ከራሳቸዉና ከአካበቢያቸው ጋር ሊያገናኛቸው የሚችል ሀሳብ፣ ኹነት፣ ክስተት ወይም መረጃ ሲሆን የህዝብ አስተያየት ጥናት፣ የሞኒተሪንግ ዉጤት፣ ወቅታዊ ትንታኔን ያካትታል፤

 

2/  ዜና ነክ መረጃዎች ማለት በዜና እንዲገለጽ የተፈለገዉን ጉዳይ ክስተት ፣ ሀሳብ ወይም ፍሬ ነገር በተለያየ አቀራረብ ለታዳሚው ለማቅረብ እንዲቻል የሚዘጋጁ ተዛማጅ፣ ተያያዥነት ያላቸው ይፋዊ የሆኑ ወይም ይፋዊ እንዲሆኑ በመረጃው ባለቤትና በህግ ፈቃድ ያላቸው መረጃዎች ናቸው፤

 

3/ “ኘሮግራም ማለት በድምፅ፣ በምስል ወይም በድምፅና በምስል ተቀነባብሮ ለማሳወቅ፣ ለማስተማር ወይም ለማዝናናት ወይም ሁሉንም አካቶ የሚቀርብ ሆኖ ስፓት ሪፓርታዥ፣ ኘሮግራምና ዘገቢ ፊልሞችን ያካትታል ፤

 

4/  ”የህትመት ስራዎች“ ማለት ለአጠቃላይ ህዝቡ ወይም ለተወሰነ አካል እንዲደርሱ ታስበው የሚሰራጩ ዘገባዎችን፣ የሞኒተሪንግ ውጤቶችን፣ አመታዊ መፅሃፎችን የሚያካትት ነው፤

 

5/   “የህዝብ አስተያየት ጥናት” ማለት ስለአንድ አገራዊና ወቅታዊ ወይም ስለአንድ ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ የህዝቡን አስተያየት፣ ግንዛቤ ወይም እርካታ ለመለካት የሚደረጉ ጥናቶችን ያካትታል ፤

 

6/   ”የማስታወቂያ ኘሮዳክሽን“ ማለት በፅሁፍ፣ በፎቶ፣ በድምፅና በምስል ተቀነባብረው የሚዘጋጁ የህዝብና የንግድ የማስታወቂያ ስራዎችን ያካትታል ፤

 

7/   ”ስነዳ ወይም ዶክሜንቴሽን“ ማለት ትልልቅ አራዊ ጉዳዮችና ክስተቶችን በፎቶ፣ በድምፅ፣ በፎቶና በተንቀሳቃሽ ምስል መቅረፅና ለወደፊት ጥቅም ላይ ሊውሉ በሚችሉበት መልኩ አሰናድቶ ማስቀመጥ ነው፤

 

8/  ክልል ማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራስያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(1)  የተመለከተው ማንኛዉም ክልል ሲሆን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮችን ይጨምራል፤

9/   በዚህ አዋጅ በወንድ ፆታ የተገለጸው ሴትንም ያካትታል።

 

3. መቋቋም

 

   1/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አገልግሎት (ከዚህ በኋላ "አገልግሎት" እየተባለ የሚጠራ) የሕግ       ሰውነት ያለው ራሱን የቻለ የመንግሥት ተቋም ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

  2/  አገልግሎቱ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል።

 

4. ዋና መሥሪያ ቤት

 

      የአገልግሎቱ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ሆኖ እንደአስፈላጊነቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ቅርንጫፎችና ወኪሎች ሊኖሩት ይችላሉ።

 

5. የአገልግሎቱ ዓላማ

 

አገልግሎቱ የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፣

1/ ኢትዮጵያ ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የምታደርጋቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አግባብ ባላቸው ፖሊሲዎችና ሕጎች መሠረት ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ማሰራጨት፤

2/ የአገሪቱን ገጽታ መገንባት፤

3/ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ዓለምአቀፍ ጉዳዮችን መዘገብ፤

4/ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ማካሄድ፣ እንደአስፈላጊነቱ ማተምና ማሰራጨት፤

5/ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ጉዳዮች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዋነኛ የዜና ምንጭ ሆኖ ማገልገል፤

6/ ዋና ዋና አገራዊ ኹነቶችንና ክስተቶችን በጽሁፍ፣ በድምጽ፣ በፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጾ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሥራዎች፣ ለምርምር ግብአትነት እንዲያገለግሉ አደራጅቶ ማስቀመጥ።

 

6. የአገልግሎቱ ሥልጣንና ተግባር

 

አገልግሎቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1/ ሃሳብና አመለካከት በነጻ እንዲንሸራሸር ለማስቻል ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የማጠናቀርና ማሰራጨት፤

2/ ከዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች ጋር ተጓዳኝ የሆኑ የፎቶግራፍና የፕሮዳክሽን አገልግሎቶችን መስጠት፤

3/ የህዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስፖት፣ ሪፖርታዥ፣ ፕሮግራምና ዘጋቢ ፊልሞችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፤

4/ ዋና ዋና አገራዊ ኹነቶችንና ክስተቶችን በጽሁፍ፣ በድምጽ፣ በፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጾ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሥራዎች፣ ለምርምር ግብአትነት እንዲያገለግሉ አደራጅቶ ማስቀመጥ፤

5/ በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያየት ጥናት የማካሄድ፣ እነዚህንም ማተምና ማሰራጨት፣

6/ ዓላማውን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉትን የራሱ የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያ ማቋቋም፤

7/ አግባብነት ካላቸው አከላት ጋር በመተባበር አስፈላጊ የሆኑትን የዜና መቀበያ፣ ማስተላለፊያ፣ ማሸጋገሪያና ማደራጃ መሣሪያዎችን በተገቢው ሥፍራዎች የማቋቋምና ማስተዳደር፤

8/ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ግንኙነት መመሥረት፤

9/ ለክልል የዜና አገልግሎት ድርጅቶች የቴክኒክና የሥልጠና ድጋፍ መስጠት፤

10/ የዜና አገልግሎት አውታሮች ስለሚስፋፉበትና በተስማሚ ቴክኖሎጂ ስለሚደራጁበት ሁኔታ እያጠና  ሃሣብ የማቅረብ፣ ሲፈቀድም በሥራ ላይ ማዋል፤

11/ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ እንደ የሕትመት፣ የጥናትና ምርምር፣ የሥልጠናና የማማከር፣ የፕሮዳክሽን፣ ኹነቶችና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እና ዘጋቢ ፊልሞች ያሉ አገልግሎቶችን ለሌሎች ተቋማት መሥጠት፤

12/ የንግድ ህጉ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝብና የንግድ የማስታወቂያ ሥራዎችን መሥራት፤

13/ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚፀድቅ ደንብ መሰረት ክፍያ ማስከፈል፤

14/ የንብረት ባለቤት መሆን፣ ውል መዋዋል፣ በሥሙ መክሰስና መከሰስ፤

 

15/ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሌሎች ተዛማች ተግባሮችን ማከናወን።

 

7. የአገልግሎቱ አቋም

 

አገልግሎቱ፡-

 

1/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቦርድ፤ (ከዚህ በኋላ "ቦርድ" እየተባለ የሚጠራ)

2/ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾም ዋና ሥራ አስፈጻሚና እንደ አስፈላጊነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፤ እና

3/ አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች ይኖሩታል።

 

8. ስለቦርዱ

 

1/ የቦርዱ አባላት ሰብሳቢውን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፤ ቁጥራቸው እንደአስፈላጊነቱ የሚወሰን ሆኖ ከአምስት ማነስ የለበትም፤

2/ የቦርዱ አባላት ስብጥር አግባብነት ከአላቸው ተቋማትና ልዩልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ይሆናል፤

3/ የቦርዱ ተጠሪነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል፤

4/  የቦርዱ የስራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል ፤

5/ የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያለድምፅ በፀሃፊነት ይሳተፋል፡፡

6/ ቦርዱ የራሱን የአሰራር መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

 

9. የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር

 

ቦርዱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1/ መገናኛ ብዙሀንን የሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ህጎች በአገልግሎቱ ተግባራዊ መደረጋቸውን ያረጋግጣል፤

2/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 እና አንቀጽ 6 የተመለከቱት የአገልግሎቱ ዓላማዎች፣ ሥልጣንና ተግባራት  ሥራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፤

3/ በአገልግሎቱ የሚዘጋጁ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጡና ትክክለኛውን አገራዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ያረጋግጣል፤

4/ በአገልግሎቱ የሚዘጋጁ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች የተለያዩ አመለካከቶችንና  አስተያየቶችን በሚያስተናግድ መልኩ መቅረባቸውን ያረጋጋጣል፤

 

5/ አገልግሎቱ ስለሚስፋፋበት ሁኔታ ፖሊሲ ይነድፋል፣ ተግባራዊነቱንም ይከታተላል፤

6/ የአገልግሎቱን ሠራተኞች ቅጥርና እድገት የሚመለከት መመሪያ ያወጣል፤ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤ የአገልግሎቱን ሠራተኞች ደመወዝ፣ አበልና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን ቦርዱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ይወስናል፤

7/ የአገልግሎቱ አሠራር የሚጠናከርበትንና የሚሻሻልበትን መንገድ ተግባራዊ ያደርጋል።

 

1. የቦርዱ ስብሰባ

 

1/ ቦርዱ ቢያንስ በሁለት ወር አንድ ጊዜ ይሰበሰባል፤

2/ አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በቦርዱ ሰብሳቢ ጥሪ ወይም ከቦርዱ አባላት መካከል ቢያንስ አንድ ሦሥተኛው ከጠየቀ በማናቸውም ጊዜ ሊሰበሰብ ይችላል፤

3/ በስብሰባው ላይ ከግማሽ በላይ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል።

4/ ቦርዱ ውሳኔ በድምጽ ብልጫ ያሳልፋል፤ ሆኖም ድምጽ እኩል ለእኩል በተከፈለ ጊዜ ሰብሳቢው ወሳኝ ድምጽ ይኖረዋል።

 

11. የዋና ሥራ አስፈጻሚ ስልጣንና ተግባር

 

1/ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከቦርዱ በሚሠጠው አጠቃላይ መመሪያ መሠረት አገልግሎቱን ይመራል፤ ያስተዳድራል፤ በዚህ አዋጅ አንቀጽ የተመለከተውን የአገልግሎቱን ሥልጣንና ተግባር ሥራ ላይ ያውላል።

2/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠተበቀ ሆኖ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣

) የአገልግሎቱን ሠራተኞች የሲቪል ሰርቪስ መርሆዎችን ተከትሎ ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይቀጥራል፤ ያስተዳድራል፤ ያሠናብታል፤

) የአገልግሎቱ ዓመታዊ የሥራ ፕሮግራምና በጀት ለቦርዱ ያቀርባል፤ ሲፈቀድም ስራ ላይ ያውላል፤

) የአገልግሎቱን ዓመታዊ ሪፖርት ለቦርዱ ያቀርባል፤

) ለአገልግሎቱ በተፈቀደው በጀትና የሥራ ፕሮግራም መሠረት ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፤

) ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ሁሉ አገልግሎቱን ይወክላል፤

) ከቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል።

 

3/ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአገልግሎቱ ሥራ ቅልጥፍና በሚያስፈልግ መጠን ሥልጣንና ተግባሩን በከፊል ለአገልግሎቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በውክልና ሊያስተላልፍ ይችላል፤ ሆኖም እርሱን ተክቶ የሚሠራው ሰው ከሠላሳ ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የሚሠራ ከሆነ ውክልናው በቅድሚያ ለቦርዱ ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል።

12. የምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ስልጣንና ተግባር

 

1/ እያንዳንዱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተመደበበትን ዘርፍ ሥራ ይመራል፤ ያስተባብራል፤ እንዲሁም የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።

2/ ዋና ስራ አስፈፃሚው በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ ይሰራል።

 

13. ሪፖርት ስለማቅረብ

 

     አገልግሎቱ በሥልጣን ክልሉ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት በየጊዜው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል።

 

14. በጀት

      የአገልግሎቱ በጀት ከሚከተሉት ምንÄች ይሆናሉ፡-

 

1.    በመንግስት የሚመደበ በጀት፤ 

2.    በዚህ አዋጅ መሠረት ከሚሰበሰበው አገልግሎት ክፍያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣው ደንብ ይወሰናል ፡፡

15. የሂሣብ መዛግብት

 

    1/ አገልግሎቱ የተሟሉና ትክክለኛ የሆኑ የሂሣብ መዛግብትና ሠነዶችን ይይዛል፤

    2/ የአገልግሎቱ የሂሣብ መዛግብትና ሠነዶች በዋናው ኦዲተር ወይም እርሱ በሚሠይማቸው ሌሎች   ኦዲተሮች በየዓመቱ ይመረመራል።

 

16. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን

 

   1/ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል።

   2/ ቦርዱ ለዚህ አዋጅ ማስፈጸሚያና ለተለያዩ የአገልግሎቱ አሰራሮች የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል።

 

17. የመብቶችና ግዴታዎች መተላለፍ

 

በደንብ ቁጥር 319/2006 ተቋቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ መብትና ግዴታዎቹ ለአገልግሎቱ ተላልፈዋል።

 

18. የተሻሩና ተፈጻሚነት የሌላቸው ሕጎች

 

    1/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲን ያቋቋመው ደንብ ቁጥር 319/2006 ተሽሮ በዚህ አዋጅ ተተክቷል፤

 

    2/ ይህን አዋጅ የሚቃረን ማንኛውም ሕግ ወይም የአሠራር ልምድ በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም።

 

19. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ

 

ይህ አዋጅ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

 

አዲስ አበባ ...... ቀን …. /2011 .

No comments:

Post a Comment